የሀገር ውስጥ ዜና

ኳታር ከኢትዮጵያ ጋር በወታደራዊ ዐቅም ግንባታ ዘርፍ በጋራ ለመሥራት ፍላጎት እንዳላት አስታወቀች

By Mikias Ayele

December 11, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኳታር እና ኢትዮጵያን ግንኙነት በይበልጥ ለማሣደግ በወታደራዊ ዐቅም ግንባታ፣ መሠረተ ልማትና ቴክኖሎጂ መስኮች በጋራ ለመሥራት ፍላጎት እንዳላቸው በኢትዮጵያ የኳታር ወታደራዊ አታሼ አስታወቁ፡፡

በኢትዮጵያ የኳታር ወታደራዊ አታሼ ብርጋዲየር ጄኔራል መሐመድ ዓሊ የተመራ የኳታር አታሼ የከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ልዑክ የመከላከያ አዛዥነትና ስታፍ ኮሌጅን ጎብኝቷል፡፡

የመከላከያ አዛዥነትና ስታፍ ኮሌጅ አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል ሙሉጌታ አምባቸው÷ ስለ ኮሌጁ አመሠራረት፣ አጠቃላይ የትምህርት አሠጣጥ ሂደትና የሌሎች ሀገራት ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮችን በማሰልጠን ለቀጣናው ሰላም እያበረከተ ያለውን አስተዋፅኦ ለልዑኩ አብራርተዋል፡፡

ኮሌጁ በ2030 ዓ.ም አሁን ካለበት በተሻለ ደረጃ ከአፍሪካ ተመራጭና ተወዳዳሪ፣ የዕውቀት እና የቴክኖሎጂ የልኅቀት ማዕከል ሆኖ መገኘት የሚል ዓላማ ይዞ እየሠራ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

የተጀመሩ ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎችን ለማሳካትም ከኳታር መከላከያ ተቋም ጋር  በትብብር ለመሥራት እንፈልጋለን ማለታቸውን ከመከላከያ ሠራዊት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

ብርጋዲየር ጄኔራል መሐመድ ዓሊ በበኩላቸው÷ የተጀመረውን የሁለትዮሽ ግንኙነት በፍጥነት ወደ ላቀ የትብብር ደረጃ ለማሣደግ በመሠረተ ልማት ግንባታ፣ በቴክኖሎጂና በሌሎች በርካታ የወታደራዊ የዐቅም ግንባታ የትብብር መስኮች ዙሪያ በጋራ ለመሥራት ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል።