አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ የሚያቀርበውን ሰብዓዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ።
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽንና የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ የ2024 የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ድጋፍ ሁኔታን በዛሬው ዕለት ይፋ አድርጓል።
የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማሪያም በዚሁ ወቅት እንደገለጹት÷ የአፍሪካ ቀንድ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ በርካታ ተግዳሮቶች እያጋጠሙት ነው።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያመጣውን ተጽዕኖ ለማቃለል የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር መተግበሯን የገለፁት ከሚሽነሩ ÷ ለራሷ ከምታደርገው እንቅስቃሴ ጎን ለጎን ከጎረቤት ሀገራት ጋር በመቀናጀትም የጋራ ጠንካራ መፍትሄ ለመስጠት እየሰራች መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ እንደ በፈረንጆቹ 2023 ለሰብዓዊ እርዳታ ያስፈልጋል ብላ በእቅድ ከያዘችው 3 ነጥብ 9 ቢሊየን ዶላር 30 በመቶ ብቻ እንዳገኘችም ነው የገለጹት።
ይህም ከእቅዱ አንጻር ሲታይ አነስተኛ መሆኑን የጠቀሱት ኮሚሽነሩ ÷ ከዚህ አንጻር ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በሰብዓዊ እርዳታ ዘርፍ ዘላቂና ተገማች የፋይናንስ ፈሰስ ማድረግ አለበት ሲሉ መጠየቃቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡