የሀገር ውስጥ ዜና

ባህላዊ የእርቅ ስርዓት የፍትህን ስርዓትን በማገዝ ረገድ ትልቅ አቅም አለው – ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር)

By Feven Bishaw

December 12, 2023

 

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባህላዊ የእርቅ ስርዓት የህብረተሰብን ማህበራዊ መስተጋብር በማጠናከር እና የፍትህን ስርዓትን በማገዝ ረገድ ትልቅ አቅም እንዳለው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) ገለፁ፡፡

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ከፍትሕ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ጋር በክልሉ በቀጣይ የፍትህ ስርዓቱን ማሻሻል እና ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል፡፡

በውይይቱ ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር)÷ የክልሉ መንግሥት የፍትህ ስርዓቱን ለማጠናከርና ፍትህን ለመስፈን በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

ይህንን ለማስጠበቅ የክልሉ መንግስት በክልሉ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋለውን የፀጥታ ችግሮችን ህብረተሰቡን በመወያየት ሰፊ ስራ በመስራት እየፈታ እንዳለም ተናግረዋል።

ባህላዊ የእርቅ ስርዓት የህብረተሰብን ማህበራዊ መስተጋብር በማጠናከር እና የፍትህን ስርዓት በማገዝ ረገድ ትልቅ አቅም እንዳለውም ርዕሰ መስተዳድሩ አመልክተዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በፍትህ ዘርፍ የሚስተዋለዉን ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በልዩ ትኩረት እንደሚሰራም መናገራቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)÷ በክልሉ የፍትህ ስርዓትን ለማሻሻልና ውጤታማ እንዲሆኑ ለማድረግ ሚኒስቴሩ አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ ገልፀዋል ።

በክልሉ የተጀመረውን የፍትህ ስርዓት ተጠናክሮ እንዲቀጥል በክልሉ የባህላዊ የእርቅ ስርዓትን በማጠናከር ውጤታማ የሆነ የፍትህ ስርዓት ማምጣት እንደሚቻልም ተናግረዋል።