የሀገር ውስጥ ዜና

የውጭ ሀገር ገንዘቦችን በማተምና ማዕድን በመያዝ ወንጀል የተከሰሱት የውጭ ሀገር ዜጎች ላይ ምስክር መሰማት ተጀመረ

By Feven Bishaw

December 12, 2023

 

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ሀገር ገንዘቦችን በማተምና የተለያየ ዓይነት ማዕድኖችን በመያዝ ወንጀል የተከሰሱት የውጭ ሀገር ዜጎች ላይ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ልደታ ምድብ 8ኛ የገቢዎችና ጉሙሩክ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ምስክር መሰማት ጀመረ።

የፍትህ ሚኒስቴር የኢኮኖሚ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ የወንጀል ተሳትፎ ጠቅሶ ተደራራቢ ሰባት ክሶችን ከአንድ ወር በፊት አቅርቦባቸዋል ነበር።

በተለይም ከ1ኛ እስከ 6ኛ ተከሳሾች ላይ ብቻ በቀረበው ክስ የወንጀል ህግ አንቀፅ 32 ንዑስ ቁጥር 1/ሀ እና አንቀጽ 356 ላይ የተደነገገውን ድንጋጌ በመተላለፍ ተከሳሾቹ ፀሀይ ሪል ስቴት ኃ/የተ/የግ/ማህበር ውስጥ 11ኛ ፎቅ ላይ በሚገኘው ቤት ውስጥ በነሃሴ 24 ቀን 2015 ዓ.ም እስከ ጳጉሜ 1 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ ሀሰተኛ ገንዘብ ለመስራት የሚያገለግሉ መሳርያዎች፣ የተለያዩ ኬሚካሎች እና ወረቀቶች በመጠቀም ሀሰተኛ የውጭ ሀገር ገንዘቦችን፣ የአሜሪካ ዶላር፣ ዩሮ፣ የእንግሊዝ ፓውንድ፣ የቻይና ዩዋን እና የሌሎች የተለያዩ ሀገራት ገንዘቦችን አመሳስለው በማተም (በመስራት)፣ ከነማተሚያ ማሽንና ለማተሚያ ከሚጠቀሙት ኬሚካሎች ጋር በመያዝ እና 104 ነጥብ 59 ግራም የሚመዝን ማግኔታይት የተፈጥሮ ማዕድን ይዞ መገኘት በሚል የተሳትፎ ደረጃ ተለይቶ ዝርዝር ክስ መቅረቡ ይታወሳል።

በተለይ 1ኛ ተከሳሽ በኮንትሮባንድ ወንጀል ክስም የቀረበበት ሲሆን፣ ሌሎቹ ማለትም ከ2ኛ እስከ 9ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱትደግሞ የፀና የመኖሪያ ፍቃድ ሳይኖር በሀገር ውስጥ መኖር የሚል የወንጀል ክስ ቀርቦባቸው ነበር።

ባጠቃላይ ተከሳሾቹ ላይ የቀረበባቸው ተደራራቢ የወንጀል ክስ በችሎት እንዲደርሳቸው ተደርጓል።

ተከሳሾቹ ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄን ተከትሎ ከዐቃቤ ሕግ ጋር ክርክር ተደርጎ ነበር።

የግራ ቀኙን ክርክር የመረመረው ችሎቱ፤ ተከሳሾቹ ላይ የቀረበው ተደራራቢና ከባድ ወንጀል መሆኑን ተከትሎ ቢወጡ ተመሳሳይ ድርጊት ላይ ሊሳተፉና ፣ ቋሚ አድራሻ ስለሌላቸው የዋስትና ግዴታቸውን አክብረው ላይቀርቡ ይችላሉ የሚለውን ግምት በመያዝና እንዲሁም ዋስትና ሊገደቡ የሚችሉባቸው የሰበር ሰሚ ችሎት ያስቀመጣቸው የድንጋጌ ነጥቦች በምክንያትነት በመጥቀስ የተከሳሾቹን ዋስትና ጥያቄ ውድቅ አድርጎ በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ ታዟል።

በዚህ መሰረት ተከሳሾቹ ከማረሚያ ቤት ዛሬ ቀርበዋል።

ተከሳሾቹ ከዚህ በፊት ወንጀሉን አለመፈጸማቸውን ገልጸው የሰጡትን የዕምነት ክህደት ቃል ተከትሎ ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን ማዳመጥ ጀምሯል።

ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ ተይዘዋል ከተባሉት ማስረጃዎች ጋር ተያይዞ ከ1ኛ እስከ 6ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾችን በሚመለከት የምስክር ጭብጡን አስመዝግቧል።

በዚህ መልኩ ፍርድ ቤቱ የሙያ ምስክሮችንም ቃል አዳምጧል።

በታሪክ አዱኛ