አዲስ አበባ ፣ ታኅሣስ 2 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ እሳት እና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ሰራተኞች ከ40 ሚሊየን ብር በላይ የአልባሳት ግዢ ጋር ተያይዞ በቀረበባቸው የሙስና ወንጀል ክስ ምስክር መስማት ተጀመረ።
ምስክር መስማት የጀመረው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።
የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ ከሁለት ወር በፊት በአጠቃላይ በስምንት ተከሳሾች ላይ ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ መመስረቱ ይታወሳል።
ክሱ የተመሰረተባቸው 1ኛ ተከሳሽ የአዲስ አበባ እሳት እና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር ሰለሞን ፍስሃ፣ 2ኛ የተቋሙ የመንግስት የግዢ ዳይሬክተር ግሩም ወልዴ፣ 3ኛ የኮሚሽኑ የለውጥ ስራ አመራር ዳይሬክቶሬት ባለሙያ ደረጄ ተፈራ፣ 4ኛ የኮሚሽኑ የሎጅስቲክስ ምዝገባና ቁጥጥር ባለሙያ ወንድሜነህ ምስጋናው፣ 5ኛ የአደጋ ስጋት ትግበራ ቡድን መሪ እዮብ ታደሰ ካሳ፣ 6ኛ በኮሚሽኑ የህክምና ባለሙያ ሲስተር አልማዝ ጌቶ፣ 7ኛ የአደጋ መረጃ ሀርድ ዌርና ሶፍትዌር ባለሙያ መስፍን ለገሰ እና 8ኛ ነጋዴ የሆኑት ንጉስ አማን የተባሉ ተከሳሾች ናቸው ።
ከእነዚህ ተከሳሾች መካከል 1ኛ እና 8ኛ ተከሳሾች በተደጋጋሚ ችሎት ያልቀረቡ መሆኑን ተከትሎ በጋዜጣ ጥሪ ከተደረገ በኋላ ባለመቅረባቸው በሌሉበት ጉዳያቸው እንዲቀጥል ብይን ተሰጥቶ ነበር።
እንደ አጠቃላይ ዐቃቤ ህግ በተከሳሾቹ ላይ የተሳትፎ ደረጃ ጠቅሶ ባቀረበው ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ላይ እንደተመላከተው ሰኔ ወር 2014 ዓ.ም በጀት አመት ከአንደኛ እስከ ሰባተኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች የግዢ ጨረታ ሂደት ውስጥ በመሳተፍ በስውር በመመሳጠር፣ በወቅቱ በተደረገ የገበያ ዳሰሳ ጥናት ቡልዶዘር የተሰኘ የእሳት አደጋ መከላከያ የአልባሳት ዋጋ በፍሬ 46 ሺህ 923 መሆኑ እየተረጋገጠ ተከሳሾቹ ግን ከፍተኛ በሆነ ዋጋ ማለትም አንዱን 184 ሺህ 644 ብር በሆነ የገንዘብ መጠን ከ8ኛ ተከሳሽ ተጫራች ድርጅት ግዢ እንዲፈጸም አፅድቀዋል በማለት በክሱ አስፍሮ ነበር።
በዚህ መልኩ አጠቃላይ 217 ፍሬ አልባሳትን በ40 ሚሊየን 67 ሺህ 748 ብር ግዢ እንዲፈጸም በማድረግ በመንግስት ላይ በልዩነት 29 ሚሊየን 885 ሺህ 441 ብር ጉዳት እንዲደርስ አድርገዋል ብሎ በክስ ዝርዝሩ ላይ ዐቃቤ ህግ ጠቅሶ ነበር።
ከተከሳሾቹ መካከል ከ1ኛ እና ከ8ኛ ተከሳሾች ውጪ ያሉት ሁሉም ችሎት ክሱ ከደረሳቸውና በችሎት ከተነበበላቸው በኋላ የዋስትና መብት ይከበር ጥያቄ አቅርበው ከዐቃቤ ህግ ጋር ክርክር ተደርጎ ነበር።
ክርክሩን የመረመረው ፍርድ ቤቱም ተከሳሾች የተከሰሱበት ድንጋጌ የዋስትና እንደማያስፈቅድ አብራርቶ የዋስትና ጥያቄያቸውን ውድቅ በማድረግ ተከሳሾቹ ማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ትዕዛዝ መስጠቱ ይታወሳል።
በተጨማሪም ተከሳሾቹ የክስ ዝርዝሩ እንዲሻሻልላቸው ባቀረቡት የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያን በሚመለከት፥ በከሳሽ ዐቃቤ ህግ በኩል ደግሞ ክሱ ግልጽ መሆኑን ጠቅሶ ክሱ ሊሻሻል አይገባም በማለት በጽሁፍ መልስ ሰጥቷል።
ፍርድ ቤቱም ክሱ እንዲሻሻል የቀረበው ጥያቄ የህግ አግባብነት የለውም በማለት ውድቅ አድርጎ ነበር።
ተከሳሾቹም በክሱ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አልፈጸምንም በማለት የዕምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል።
ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ህግ ምስክሮችን ቃል ለመስማት በሰጠው ተለዋጭ ቀጠሮ መሰረት ዛሬ በችሎት ተሰይሞ የምስክር ቃል መስማት ጀምሯል።
ዐቃቤ ህግ በግዢ ሥነ ሥርዓት፣ በጨረታ መመሪያና በገበያ ዳሰሳን ጨምሮ የአልባሳት ጥራትን በሚመመለከት ከ2ኛ እስከ 7ኛ ተራ ቁጥር በተጠቀሱ የጨረታ ኮሚቴ ነበሩ የተባሉ ተከሳሾች ላይ የምስክር ጭብጥ አስመዝግቦ ነው ምስክር መስማት የተጀመረው።
በታሪክ አዱኛ
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!