አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ሥደተኞችን የሚመለከቱ ዓለም አቀፍ ግቦችን በመፈፀም ለውጥ አምጥታለች ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለፁ፡፡
በአቶ ደመቀ መኮንን የተመራ ልዑክ በስዊዘርላንድ ጄኔቫ እየተካሄደ በሚገኘው 2ኛው ዓለም አቀፍ የሥደተኞች ፎረም ላይ እየተሳተፉ ነው፡፡
አቶ ደመቀ በመድረኩ ባደረጉት ንግግር÷ በ2011 ዓ.ም የተካሄደው የዓለም አቀፍ የሥደተኞች የምክክር መድረክ ላይ የተቀመጡትን የስራ፣ ትምህርት፣ ከለላ የመስጠት፣ ሃይል ልማት እና የአካባቢ ጥበቃ ግቦችን በከፍተኛ ሁኔታ ማሳካት መቻሉን ገልጸዋል።
የአየር ንብረት ለውጥን አሉታዊ ተፅዕኖዎች ለመቅረፍ ችግኞችን መትከል እና አማራጭ የሃይል ምንጮችን ማቅረብ፣ ሁለት የሥደተኛ መጠለያ ጣቢያዎችን ወደ ከተማ ማሳደግን ጨምሮ 6 አዳዲስ ግቦችን ኢትዮጵያ መተለሟን አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ከለላ የሚሹ ሰዎችን ለመቀበል ያላትን የረጅም ጊዜ ቁርጠኝነት አረጋግጠው÷ በአሁኑ ወቅት ከአንድ ሚሊየን በላይ ሥደተኞችን እያስተናገደች እንደሆነ መጠቆማቸውንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡