የሀገር ውስጥ ዜና

አቶ አብነት ገ/መስቀል የተከሰሱበትን የሙስና ወንጀል ድርጊት እንዳልፈጸሙ በመግለጽ የዕምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጡ

By Melaku Gedif

December 13, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አቶ አብነት ገ/መስቀል የተከሰሱበትን የሙስና ወንጀል ድርጊት አለመፈጸማቸውን ገልጸው የዕምነት ክህደት ቃላቸውን ለፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሙስና ወንጀል ችሎት ሰጡ።

ችሎቱ ዛሬ አቶ አብነት ያቀረቡትን የክስ መቃወሚያና የዐቃቤ ሕግ መልስን መርምሮ ብይን ሰጥቷል።

የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት አቶ አብነትን ጨምሮ በአምስት ተከሳሾች ላይ አቅርቦት በነበረው ክስ ላይ እንዳመለከተው አቶ አብነት ገ/መስቀል በቂርቆስ ክ/ከ ወረዳ 2 የሚገኘውን ከሼክ አላሙዲን መሀመድ ጋር የጋራ ንብረታቸው የሆነውን የ1 ሺህ 971 ካሬ ሜትር ይዞታ ከሌሎች ተከሳሶች ጋር በመመሳጠር ቦታው ላይ ካርታ በማዘጋጀት ይዞታውን በ83 ሚሊዮን ብር በመሸጥ ያለአግባብ መብት ተፈጥሮላቸዋል በሚል ነበር።

በሁለተኛው ክስ ደግሞ በህገወጥ መንገድ የተገኘ ንብረትን ወይም ገንዘብን ህጋዊ አድርጎ ማቅረብ የሚል ክስ ነበር የቀረበው።

ክሱ ከተመሰረተባቸው ተከሳሾች መካከል አቶ አብነትና 5ኛ ተከሳሽ የአ/አ ከተማ አስተዳደር የመሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ቂርቆስ ቅርጫፍ የመብት አገልግሎት ቡድን መሪ ወንድማገኝ ዳኛው የተባሉ ተከሳሽ ችሎት ቀርበዋል።

ቀሪ 2ኛ፣ 3ኛ እና 4ኛ ተራ ቁጥር ላይ የተጠቀሱት ተከሳሾች ችሎት አልቀረቡም።

በዚህ ክስ ዝርዝር ላይ በአቶ አብነት ጠበቆች በኩል የክሱ አቀራረብ የወንጀል ህጉን የተከተለ አደለም የሚሉና የወንጀል ማቋቋሚያ ፍሬ ነገርን በሚመለከት፣ ጉዳዩ የፍትሐብሔር እንጂ የወንጀል ጉዳይ አይደለም የሚሉና ማስረጃን የሚመለከቱ ነጥቦች ጠቅሰው፤ ክሱ እንዲሻሻልላቸው የክስ መቃወሚያ አቅርበው ነበር።

ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ ክሱ ሊሻሻል እንደማይገባ በመግለጽ መልስ ሰጥቷል።

ፍርድ ቤቱ ግራ ቀኙን መርምሮ ብይን ለመስጠት ለዛሬ በሰጠው ተለዋጭ ቀጠሮ መሰረት የቀረበው የክስ መቃወሚያ ጥያቄ አግባብነት እንደሌለው በመግለጽ ውድቅ አድርጎታል።

የዐቃቤ ሕግ ይካተትልኝ ያለውን የሰነድ ማስረጃ በሚመለከት ጠበቆች ባቀረቡት መከራከሪያ ማለትም ከሚድሮክ ኩባንያ የሚቀርበው የሰነድ ማስረጃ በአንድ ወገን ብቻ የቀረበ መሆኑ ተገቢነት የለውም በማለት በመቃወም ተከራክረዋል።

ፍርድ ቤቱ የቀረቡ ሀሳቦች በማስረጃው ሊመረመርና ሊታረም፣ ሊመዘን የሚችል መሆኑን ጠቅሶ የቀረቡ ማስረጃዎች እንዲያያዙ ብይን ሰጥቷል።

አቶ አብነት ገ/መስቀል በተከሰሱበት በሁለቱም ክስ ላይ የተጠቀሰውን የሙስና ወንጀል ድርጊት አለመፈጸማቸውን ገልጸው የዕምነት ክህደት ቃላቸውን አስመዝግበዋል።።

በተጨማሪም በ5ኛ ተከሳሽ የቀረበ የክስ መቃወሚያን በፅሁፍና በሲዲ በመረከብ ከቀጠሮ በፊት ዐቃቤ ሕግ መልስ እንዲሰጥበት አዟል።

ያልቀረቡ ተከሳሾችን በሚመለከትና የ5ኛ ተከሳሽ የክስ መቃወሚያ ላይ ብይን ለመስጠት ለታህሳስ 12 ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

የዐቃቤ ሕግ 8 ምስክር አሰማምን በሚመለከት በቀጣይ ቀጠሮ ትዕዛዝ እንደሚሰጥበት ፍርድ ቤቱ ገልጿል።

በታሪክ አዱኛ