አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ኢትዮጵያውን ለማህበረሰባቸው ችግሮች የመፍትሄ አቅራቢዎች እንዲሆኑ ለማስቻል የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፍ አስታወቀ።
በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) የተመራ ልዑክ ከተመድ ምክትል ዋና ፀሃፊና የድርጅቱ የሴቶች ጉዳይ ዋና ፀሃፊ ሲማ ባሆስ ጋር መክሯል።
ውይይቱ ወላጆቻቸውን ያጡ ህፃናት፣ አቅመ ደካሞችንና ሴቶችን መደገፍና የጋራ ራዕይን መያዝ ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል።
በውይይቱ ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)÷ ኢትዮጵያውያን በማህበረሰባቸው ውስጥ ላሉ ችግሮች የመፍትሄ አቅራቢዎች ሆነው እንዲያገለግሉ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህንን ጥረት ተመድ እንዲደግፍ የጠየቁት ሚኒስትሯ፤ ድርጅቱ በሌሎች ፕሮግራሞች እያደረገ ስላለው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
በተመድ የሴቶች ጉዳይ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሲማ ባሆስ÷ የኢትዮጵያ መንግስት በተለይም የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አዳዲስ አሰራሮችን በመዘርጋት የሴቶችን ህይወት ለማሻሻል የሚያደርገውን ጥረት አድንቀዋል።
የበጎ ፈቃድ ማሳደጊያ ፕሮግራሙን ለመደገፍም ፍላጎት እንዳላቸው ማረጋገጣቸውን ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡