የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ አየር ኃይል ከአፍሪካ ሀገራት ጋር በትብብር ለመሥራት ዝግጁ ነው – ሌ/ጄ ይልማ መርዳሳ

By Shambel Mihret

December 14, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር ኃይል በሁሉም ዘርፎች ከአፍሪካ ሀገራት ጋር በትብብር ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን የአየር ኃይሉ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ።

የመጀመሪያው የአፍሪካ አየር ኃይል አዛዦች ፎረም በቢሾፍቱ እየተካሄደ ሲሆን÷ በፎረሙ የአፍሪካ ሀገራት አየር ኃይል አዛዦች፣ የተለያዩ አገራት የአቪዬሽን ተቋማት ኃላፊዎችና ወታደራዊ አታሼዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል 88ኛ ዓመት የምስረታ በዓል “በመስዋዕትነት ሀገርን የዋጀ የኢትዮጵያ አየር ኃይል” በሚል መሪ ሃሳብ ከሕዳር 20 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ እየተከበረ ይገኛል።

የመርሐ ግብሩ አካል በሆነው በዚህ የአፍሪካ አየር ኃይል አዛዦች ፎረም ላይ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ እንደገለጹት÷ አየር ኃይሉ በርካታ የአፍሪካ ሀገራትን በአየር ኃይል፣ በልምምድና በአየር ትራንስፖርት ዘርፎች እገዛ ሲያደርግ ቆይቷል።

እገዛውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠው፤ የኢትዮጵያ አየር ኃይል በቀጣይም የጀመራቸውን ሥራዎች ይበልጥ በማጠናከር በሁሉም ዘርፎች ከአፍሪካ ሀገራት ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁነቱን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በፎረሙ በአፍሪካ የአየር ኃይል ዕድገት ላይ ሊገጥም የሚችሉ ተግዳሮቶችን በጋራ መፍታት በሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች ዙሪያ ምክክር ይደረጋል ተብሏል።