የሀገር ውስጥ ዜና

በአዲሱ ክልል ለዓመታት ሲነሱ ለነበሩ የሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ ተሰጥቷል – አቶ እንዳሻው ጣሰው

By Melaku Gedif

December 14, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሕብረተሰብ አቀፍ ክልላዊ የምክክር መድረክ በሆሳዕና ከተማ እየተካሔደ ነው

የክልሉ ም/ርዕሰ መስተዳደር እንዳሻው ጣሰው በዚህ ወቅት እንደገለጹት÷ በአዲሱ ክልል ለረጅም ዓመታት ሲቀርቡ የነበሩ የዞንና የልዩ ወረዳ መዋቅር ጥያቄዎች ምላሽ አግኝተዋል።

በተለያየ ደረጃ ከሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር በክልሉ ነባራዊ ሁኔታ ላይ ውይይት በመደረጉ ለክልሉ መንግስት በቂ ግብዓት ማግኘት መቻሉን ተናግረዋል።

በክልሉ መንግስት ምስረታ ወቅት የተለያዩ አዋጆች፣ደንቦች እንዲሁም የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ሹመት መጽደቁን ጠቁመዋል።

ከዚህ ቀደም የአመራር ውክልና የማይደርሳቸው አካባቢዎችን ታሳቢ ያደረገ የአመራር ምደባ ማካሔድ መቻሉንም ጠቁመዋል።

በክልሉ የመንግስት እና የመሪውን ፓርቲ የመቶ ቀናት እቅድ በማዘጋጀት ወደ ተግባር መገባቱን ርዕሰ መስተዳድሩ በንግግራቸው አውስተዋል።

በክልሉ የተጀመሩ የልማት፣ የመልካም አስተዳደር እና የሰላም ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የመቶ ቀናት እቅዱ አካል እንደተደረገ መናገራቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

በክልሉ ለህብረተሰቡ የሚሰጠውን አገልግሎት ውጤታማ ለማድረግ በ7 ማዕከላት ስራ የማስጀመር ተግባር ማከናወን እንደተቻለም አስታውሰዋል።

የክልሉ መንግስት በይፋ ስራ በጀመረ ማግስት ፣የሰላምና ጸጥታ፣የግብርና፣የገቢ፣የትምህርት እና የጤና ሴክተር ስራዎች ላይ ትኩረት መደረጉን ጠቅሰዋል።

በሁሉም ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች የህዝብ ውይይት በማድረግ የተገኘውን ግብዓት የክልሉ መንግስት የስራ እቅድ አካል እንዲሆን መሰራቱንም አብራርተዋል።