የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉን የስደተኞች መርህ በመከተል ለስደተኞች ድጋፍ እያደረገች ነው ተባለ

By Shambel Mihret

December 14, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉን የስደተኞች መርህ በተከተለ መንገድ ለስደተኞች ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እያደረገች መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ገለጹ።

ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)÷ ከሁለተኛው የዓለም አቀፍ የስደተኞች ፎረም ጎን ለጎን ከኔዘርላንድስ የውጭ ንግድና ልማት ትብብር ምክትል ሚኒስትር ፓስካል ግሮተንሁይስ እና የዴንማርክ የልማት ፖሊሲ ዋና ፀሃፊ ሎተ ማቾን ጋር ውይይት አካሂደዋል፡፡

በውይይታቸውም÷ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉን የስደተኞች መርህ ተከትላ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ለስደተኞች ማድረጓን ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ስለተገበረችው የኢኮኖሚ ማሻሻያ እና ስላስመዘገበችው ውጤት እንዲሁም የጋራ ብልጽግናን ማረጋገጥ ስለሚቻልበት ሁኔታም ገለጻ አድርገዋል።

በኢትዮጵያና በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የቆየ ትብብር አድንቀው÷ የዓለም አቀፍ የስደተኞች ፎረም ስደተኞች ሰርተው የሚለወጡበትን እድል መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡

የኔዘርላንድስ የውጭ ንግድና ልማት ትብብር ምክትል ሚኒስትር ፓስካል ግሮተንሁይስ እና የዴንማርክ የልማት ፖሊሲ ዋና ፀሃፊ ሎተ ማቾን÷ ኢትዮጵያ ለስደተኞች ዓለም አቀፍ ጥበቃና መፍትሄ በመስጠት ያላትን የመሪነት ሚና አድንቀዋል።

ከኢትዮጵያ ጋር በስደተኞች ጉዳይ ላይ በሁለትዮሽ እና በባለብዙ ወገን ትብብር በጋር ለመስራት ያላቸውን ቁርጠኝነትም እንደገለጹ ኢዜአ ዘግቧል፡፡