አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሐረር ከተማን ለነዋሪዎቿ ምቹና ለጎብኚዎች ተመራጭ ለማድረግ የሚከናወኑ ውጤታማ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ተናገሩ፡፡
የጁገል ዓለም አቀፍ ቅርስ ውስጥ ለውስጥ መንገዶች እንክብካቤና ልማት 1ኛ ዙር ምረቃና ሁለተኛው ዙር ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድሩ ከለውጡ ወዲህ በተሰሩ ስራዎች ሐረር በዓለም የቅርስ ከተሞች ድርጅት አባል ሆና እንድትመዘገብ ከማድረግ ባለፈ የሸዋል ኢድ ክብረበዓል በዩኔስኮ በማይዳሰስ ቅርስነት ማስመዝገብ ተችሏል ብለዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህም እየተሰሩ የሚገኙ የአረንጓዴ ልማትና የከተማ ፅዳትና ውበት ስራዎች ለነዋሪዎቹ ምቹና በጎብኚዎች ተመራጭ ከተማ ለማድረግ እንደሚቻል ያመላከተ እንደሆነም ነው የገለጹት።
ሐረር ያላትን መስህብ በመንከባከብና በማልማት ረገድ በተለይም የዓለም ቅርስ የሆነውን የጁገል ቅርስ ከአደጋ ለመታደግና ለማልማት ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡
ለዚህም ቀደም አደጋ ተጋርጦበት የነበረውን የጁገል ዓለም አቀፍ ቅርስ ለመታደግ በዙሪያው ሲካሄዱ የቆዩ ህገወጥ ግንባታዎችን በመከላከል ቅርሱን የመጠበቅና የመንከባከብ ስራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋልም ነው ያሉት።
ህዝቡን በንቃት በማሳተፍ የተሰሩ ስራዎች ውጤት ማምጣታቸውን ጠቅሰው፥ በቀጣይም እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
በቀጣይ ህዝብን ባለቤት ባደረገ መልኩ በመንቀሳቀስ ስራዎቹን ዘላቂ እንዲሆኑም በማድረግ ረገድ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት።
በተጨማሪም ዳያስፖራውን፣ ባለሃብቶችን፣ የንግዱ ማህበረሰብና ሌሎች አካላትን በማሳተፍ የተጀመሩ ስራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ አመላክተዋል።
የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን በማልማት ረገድም እየተሰሩ የሚገኙ ስራዎች እንዲጎለብቱ ትኩረት እንደሚሰጥም ነው የገለጹት፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይም የጁገል ዓለም አቀፍ ቅርስ ውስጥ ለውስጥ መንገዶች እንክብካቤና ልማት ስራ ላይ የላቀ አፈፃፀም ላበረከቱ አካላት ሽልማትና እውቅና እንደተሰጠ የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል።