የሀገር ውስጥ ዜና

የኮንትሮባንድ ንግድ የታክስ አሰባሰብ ስርዓቱን እየተፈታተነው መሆኑ ተገለፀ

By Meseret Awoke

December 15, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የወጪ እና ገቢ ኮንትሮባንድ ንግድ በየጊዜው መልኩን እየቀያየረ የንግድ ስርዓቱን በማዛባት የታክስ አሰባሰብ ስርዓቱን እየተፈታተነው ይገኛል ሲሉ የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ ገለጹ፡፡

በታክስ አሰባሰብ እና ህገወጥነትን መከላከል ዙሪያ የሚመክር ውይይት እየተካሄደ ሲሆን በውይይቱ የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ ፥ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ በአግባቡ በመሰብሰብ ሀገራዊ ወጪን በታክስ ገቢ ለመሸፈን እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ባለፉት የለውጥ ዓመታትም በፌዴራል፣ በክልሎችና ከተማ አስተዳደር ገቢ ሰብሳቢ ተቋማት መካከል የታክስ አስተዳደር ስርዓቱን ለማጣጣምና ለማጠናከር የታክስ ፖሊሲ እና የህግ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን ሚኒስትሯ አስረድተዋል፡፡

እነዚህ ማሻሻዎችም ለገቢ አሰባሰቡ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውንም ነው የገለጹት፡፡

ከታክስ እና ቀረጥ የሚገኘው ገቢ በየአመቱ በአማካይ በ23ነጥብ 8 በመቶ እያደገ መምጣቱን የተናገሩት ወ/ሮ ዓይናለም ፥ የታክስ ገቢው ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት ጥምርታ አንጻር ሲታይ ግን ጉድለቶች መኖራቸውን አስረድተዋል፡፡

ያለደረሰኝ ግብይት፣ የሀሰተኛ ደረሰኞች ስርጭት፣ ከዋጋ በታች የሚሰጡ ደረሰኞች መበራከት፣ የኮንትሮባድ ንግድ ሰንሰለት ውስብስብ መሆን፣ የህገወጥ ንግድ እና የህቡዕ ኢኮኖሚ መስፋፋት ለታክስ አሰባሰብ ስርዓቱ ዋነኛ ማነቆዎች መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትሯ አክለውም ፥ የወጪ እና ገቢ ኮንትሮባንድ ጉዳይ በየጊዜው መልኩን እየቀያየረ የንግድ ስርዓቱን በማዛባት የታክስ አሰባሰብ ስርዓቱን እየተፈታተነው እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡

ችግሩን ለመቀነስም ከላይ እስከታች ያለውን የቁጥጥር ስርዓት መፈተሸና ማጠናከር እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡