የሀገር ውስጥ ዜና

በአማራ ክልል የአመራር መልሶ ማደራጀት ተግባር ሰላም ለማስፈን ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ተባለ

By ዮሐንስ ደርበው

December 15, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል እስከ ወረዳ ድረስ የተካሄደው የአመራር አባላት መልሶ ማደራጀት ተግባር ሰላምን በዘላቂነት ለማስፈን ምቹ ሁኔታ መፍጠሩ ተገለጸ።

በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የ2016 በጀት ዓመት ያለፉትን አምስት ወራት የሥራ አፈፃፀም ግምገማና የቀሪ ወራት የሥራ አቅጣጫ ላይ በባሕርዳር ከተማ እየተወያየ ነው።

በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ተፈጥሮ የነበረውን የጸጥታ ችግር ፈጥኖ በመቀልበስ ወደ ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማሸጋገር የፖለቲካና የጸጥታ አመራር አባሉን መልሶ የማደራጀት ሥራ ሲከናወን መቆየቱን የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ይርጋ ሲሳይ አስታውሰዋል፡፡

በዚህም ከክልል እስከ ወረዳ ድረስ የአመራር አባላትን መልሶ በማደራጀት በቁርጠኝነት በተካሄደው ትግል ሰላምን በዘላቂነት ለማስፈን ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል፡፡

በክልሉ የተገኘውን ሰላም በዘላቂነት አጽንቶ ለማስቀጠልም የፖለቲካ አመራር አባላት ተልዕኳቸውን በቁርጠኝነት እንዲፈጽሙ አሳስበዋል፡፡

በክልሉ የተካሄደው የመልሶ ማደራጀት ተግባርም በተሳካ ሁኔታ ተፈጽሞ አሁን የተገኘው ለውጥ እንዲመጣ የመከላከያ ሠራዊት ለከፈለው መስዋዕትነት ምስጋና ይገባዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በቀጣይም የፖለቲካና የጸጥታ መዋቅሩን አደረጃጀት በማጠናከር በክልሉ የሕግ የበላይነትና ሰላም ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!