የሀገር ውስጥ ዜና

ትውልድ ከዓለም ዕድገት ጋር እንዲራመድ የሚሰጠው ትምህርት ጥራት ያለው መሆን ይጠበቅበታል – አቶ ደስታ ሌዳሞ

By Meseret Awoke

December 15, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ትውልድ ከዓለም ዕድገት ጋር እንዲራመድ በየትኛውም ደረጃ የሚሰጠው ትምህርት ጥራት ያለዉና ተወዳዳሪ የሚያደርግ መሆን ይጠበቅበታል ሲሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ይህንን ያሉት የክልሉ ትምህርት ቢሮ ባካሄደው 3ኛ ዓመታዊ የትምሀርት ጉባዔ ላይ ነዉ።

አሁን የገጠመንን የትምህርት ጥራት ችግር ለመቅረፍና ብቁ ዜጎችን ለመፍጠር የትምህርት ዘርፍ ተዋናዮች ሁሉ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት አለባቸው ሲሉም አሳስበዋል።

የትምህርት ዘርፍ አካላት ትውልዱ ከተሳሳተ የትምህርት ፅንሰ ሀሳብና ከተቀጣሪነት አመለካከት የሚወጣ፣ ፈተናዎችን ወደ እድል የሚቀይር እንዲሁም በዙሪያው ያሉትን መልካም አጋጣሚዎች እንዲጠቀም በትጋት መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የዘርፉን ችግሮች ለመቅረፍ ሁሉም አመራር የትምህርት ጉዳይ የሚያሳስበውና ለችግሮቹ እልባት ለመስጠት የሚተጋ መሆን አለበትም ሲሉ ነዉ የገለፁት።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ በየነ በራሳ ትምህርትን ከችግር ለማዉጣት የትምህርት ተቋማትን ማሻሻልና አዳዲስ መገንባት፣ የትምህርት ግብዓት ማቅረብና ማከፋፈልና የመምህራን ብቃት ላይ ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።

በተለይ የትምህርት ተቋማት ግንባታ ላይ የግሉም ዘርፍ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

በክልሉ ባለሃብቶችና ሰራተኞች አስተዋጽዖም 100 ትምህርት ቤቶች ለመገንባት ታቅዶ እስካሁን 49 ተጠናቀዋል ብለዋል።

ከደረጃ በታች የሚገኙ መደበኛ ትምህርት ቤቶች 95 ነጥብ 8 በመቶ መሆናቸው ገልጸው፥ ከእነዚህ ውስጥ 73 ነጥብ 4 በመቶ ደግሞ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንደሆኑም ነው የተገለጸው፡፡

በቢቂላ ቱፋና ደብሪቱ በዛብህ

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!