የሀገር ውስጥ ዜና

የገንዘብ ሚኒስቴር ሁሉንም የዩሮ ቦንድ አበዳሪዎች በእኩልነት እንደሚያስተናግድ ይፋ አደረገ

By Tamrat Bishaw

December 15, 2023

አዲስ አበባ ፣ ታኅሣስ 5 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የገንዘብ ሚኒስቴር ከዩሮ ቦንድ አበዳሪ ባለድርሻ አካላት ጋር ዓለም አቀፍ የባለሃብቶች ውይይት አካሂዶ ሁሉንም አበዳሪዎች በእኩል ሁኔታ እንደሚያስተናግድ ይፋ አደርጓል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በበይነ መረብ በተካሄደና ከ100 በላይ ተሳታፊዎች በተገኙበት ውይይት ስለሀገሪቱ ወቅታዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታ፣ ከልማት አጋሮችና ከውጪ አበዳሪዎች ጋር ስለተደረጉ የዕዳ ሽግሽግ ውይይቶች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ሀገሪቱ ከጋራ ማዕቀፍ የዕዳ ሽግሽግ ቀድሞ ከዩሮ ቦንድ አበዳሪዎች ጋር የዕዳ ክፍያ ሽግሽግ ለማድረግ ያላትን ዕቅድ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ በቅርቡ ከታወቁ አበዳሪዎች ጋር የዕዳ ክፍያ ሽግሽግ ለማድረግ ሥምምነት ላይ መድረሷ የሚታወቅ ሲሆን፥ በዚህም መሰረት የገንዘብ ሚኒስቴር የዩሮ ቦንድን ጨምሮ ከሌሎች የግል አበዳሪዎች ጋር ውይይት በመጀመር ሀገሪቷ ወጥነት ያለው የዕዳ ሽግሽግ እንዲደረግላት ጥረቱን ቀጥሏል።

በዚህም መሰረት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) የታህሣሥ ወር የዩሮ ቦንድ ወለድ ክፍያን ሀገሪቷ ላለመክፈል የወሰነችበትን ምክንያት አብራርተዋል፡፡

ምንም እንኳን የክፍያ መጠኑ በአሁኑ የሀገሪቷ አቅም መክፈል የሚቻል ቢሆንም ላለመክፈል የተወሰነው ሁሉንም አበዳሪዎች በእኩል ሁኔታ ማስተናገድ አስፈላጊ በመሆኑና ከሌሎች አበዳሪዎች ጋር እየተካሄዱ ያሉ ውይይቶች እንዳይደናቅፉ በማሰብ መሆኑን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዕቅድ የቦንድ ባላቤቶችን ከወዲሁ በማሳተፍ ለአንድ ጊዜና ለመጨረሻ ጊዜ የውጪ ብድር ችግሮችን መፍታት ሲሆን፥ ይህ አካሄድም የኢትዮጵያ የጋራ ማዕቀፍ የዕዳ ሽግሽግ ውይይቶች ሙሉ በሙሉ ወደ ተግባር እስከሚሸጋገሩ ድረስ የቦንድ ባለቤቶችም የተሻለ የቦንድ ዋጋ ይዘው እንዲቆዩ የሚያስችል ነው ተብሏል።

ለዩሮ ቦንድ አበዳሪዎች የቀረበው የዕዳ ሽግሽግ ምክረ ሀሳብ የተነደፈው የጋራ ማዕቀፍ የብድር ሽግሽግ ሲጀመር ሊያጋጥም የሚችለውን የድጋሚ ሽግሽግ ጥያቄ እንዳይፈጠር ታሳቢ በማድረግ መሆኑም ተነስቷል።

ይህ ሽግሽግ መደረጉ በቦንዱ ባለቤቶች ላይ የሚያሳድረው ስጋት እንዳለ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚረዳ ሆኖ እነዚህን ስጋቶችን ለመቀነስም የመፍትሔ አቅጣጫዎች ለተሳታፊዎች ቀርበዋል።

የገንዘብ ሚኒስቴር ከሁሉም አበዳሪዎች ጋር ያለውን ግንኙነት ጤናማ ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝነት በድጋሜ ገልጾ በግልጸኝነት፣ በተዓማኒነትና በፍትሀዊነት መንፈስ ከሁሉም አበዳሪዎች ጋር ለመወያየት ያለውን ዝግጁነት ማሳወቁን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

የውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች ጥያቄ ፣ ሀሳብና አስተያየት አቅርበው ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በስፋትና በጥልቀት የተወያዩ ሲሆን፥ ተጨማሪ ጥያቄዎች በቀረበው ምክረ ሀሳብ ላይ ያላቸውን አስተያየት በኢ-ሜል አድራሻ፡ eth.investors@lazard.com ላይ እንዲያቀርቡ ተጋብዘዋል።