የሀገር ውስጥ ዜና

የባቡር ደህንነት ተግዳሮቶችና የመፍትሔ ሀሳቦች ላይ ያተኮረ ምክክር እየተካሄደ ነው

By Feven Bishaw

December 16, 2023

 

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 6 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የባቡር ደህንነት ተግዳሮቶችና የመፍትሔ ሀሳቦች ላይ ያተኮረ ምክክር በድሬዳዋ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

በውይይቱ የኢትዮ ጁቡቲ ባቡር የገቢ ወጪ ንግድ በማስተናገድ ለኢትዮጵያ መሠረት ስለመሆኑ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚኒስትሩ አለሙ ስሜ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

በመሆኑም የኢትዮ ጁቡቲ ባቡር መንገድ ደህንነትን የመጠበቅ ስራ የሉዓላዊነት ጉዳይ ያደርገዋል ነው ያሉት።

በሌላ በኩል የመንገድ መዝጋት፣ ስርቆት፣ የትራፊክ አደጋዎች ለኢትዮ ጁቡቲ ባቡር መንገድ ዋነኛ ተግዳሮት መሆናቸው በውይይቱ ተነስቷል።

ጥቃቱን ከመከላከል አንፃር ባቡሩ የሚያልፍባቸው ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ሀላፊነት በመውሰድ መስራት እንደሚጠበቅባቸውም አመላክተዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር በባቡር ስርቆት ላይ በሰራው ሥራ የስርቆት ምጣኔውን በአንፃራዊነት መቀነስ መቻሉ ተገልጿል።

ሌሎችም ይህን ተሞክሮ በመውሰድ በባቡር ላይ የሚደረጉ ስርቆቶችን ማስቆም እንደሚገባቸው ተጠቁሟል።

የትራንስፖርትና ሎጂስትክ ሚኒስትርም ችግር የሚከሰትባቸውን ስፍራዎች በመለየት ተጠያቂነትን ለመዘርጋት ማቀዱን አስታውቀዋል።

በኢዮናዳብ አንዱአለም