የሀገር ውስጥ ዜና

የአየር ሀይል የውጊያ ዝግጁነት ከንግግር ባለፈ በተግባር ወደ ላቀ ደረጃ ደርሷል – ሌ/ጄ ይልማ መርዳሳ

By Shambel Mihret

December 16, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር ሀይል የውጊያ ዝግጁነት ከንግግር ባለፈ በተግባር ወደ ላቀ ደረጃ ደርሷል ሲሉ የአየር ኃይሉ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ

ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ የአየር ኃይሉ 88ኛ ዓመት የምስረታ በዓል የማጠቃለያ መርሐ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር÷ አየር ሃይሉ በተለያዩ መንግስታዊ ስርዓቶች በርካታ ውጣ ውረዶችን እንዳሳለፈ ተናግረዋል፡፡

አየር ሀይሉ ለሀገር ሉዓላዊነትና አንድነት በየጊዜው ወርቃማ ገድሎችን እንደፈጸመ ጠቅሰው÷ በአጭር ጊዜና በቀላሉ የሚገነባ ተቋምም አለመሆኑን አንስተዋል፡፡

በ1983 ዓ.ም የመንግስት ለውጥ ሲደረግ ተቋሙ ሙሉ በሙሉ ፈርሶ ሰራዊቱም ተበትኗል ያሉት ዋና አዛዡ÷ ይሄም አየር ሀይሉን በብዙ አስርት አመታት ወደ ኋላ እንዲመለስ አድርጎታል ነው ያሉት፡፡

ከዚህ በፊት የአየር ሀይሉ ቀን በዘፈቀ ሲከበር እንደነበር አስታውሰው÷ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የተዛቡ ታሪኮችን የማረምና የማስተካከል ስራ በመሰራቱ የአየር ሃይሉ ምስረታ ትክክለኛ ቀንን በማጥናት ታሪኩን ጠብቆ እንዲከበር ለማድረግ አስችሎናል ብለዋል፡፡

በዚህም ሕዳር 20 ቀን 1928 የአየር ሀይል ምስረታ ቀን ሆኖ እንዲከበር መወሰኑን በመግለጽ፤ የምስረታ ቀኑም ከሕዳር 20 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ “በመስዋዕትነት ሀገርን የዋጀ የኢትዮጵያ አየር ሀይል” በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች ሲከበር መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡

በዛሬው እለትም 88ኛው የኢትዮጵያ አየር ኃይል የማጠቃለያ መርሐ ግብር እየተካሄደ መሆኑን ገልጸው÷ ለተቋሙ አመራሮችና ለሰራዊቱ አባላት እንኳን አደረሳችሁ ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የተቋሙን የሰው ሀይል ፍላጎት ከማሟላት ባሻገር ለሌሎች የሀገር ውስጥ ተቋማትና ለውጭ ሀገር ወዳጅ ሀገሮችም የሙያተኛ ድጋፍ እያደረግን እንገኛለን ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል በጉብኝት ለህዝቡ እና ለተቋሙ ግልጽ ያደረግናቸውና በአየር ትርኢት የታዩ ትጥቆች ከአምስት አመት በፊት አልነበሩም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የነበሩትም ተጥለው አቧራና ዳዋ የበቀለባቸው እንደነበሩ ገልጸው፤ በተቋሙ ሪፎርም ከተያዙ ግቦች አንዱ ትጥቆቻችንን በውስጥ አቅማችን በማሻሻል የተቋሙን ውጊያ ዝግጁነት በፍጥነት ወደላቀ ደረጃ ማድረስ የሚል ነው ብለዋል፡፡

በዚህም በርካታ ትጥቆች እድሳትና ማሻሻያ እንደተደረገላቸው ጠቅሰው÷ የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግርንም በተግባር አረጋግጠናል ነው ያሉት፡፡

የአየር ሀይል የውጊያ ዝግጁነት ከንግግር ባለፈ በተግባር ወደ ላቀ ደረጃ ደርሷልም ብለዋል ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ፡፡