የሀገር ውስጥ ዜና

ሰው በማገት 10 ሚሊየን ብር የጠየቁ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

By Mikias Ayele

December 17, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አንድን ወጣት አግተው 10 ሚሊየን ብር የጠየቁ ሁለት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት÷ የአዲስ አበባ ፖሊስ፣ ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት እና የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ ባደረጉት ክትትል መሆኑ ተገልጿል፡፡

አጋችና ታጋች የአንድ ወር ጓደኛሞች እንደነበሩም ነው የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ ያመላከተው፡፡

ባንቴ ይድረስ የተባለው ግለሰብ የወንድሜን ጓደኛ ቤት ላሳይህ በማለት ታጋች ልዑል መብራቱ ጸጋዬን ታኅሣስ 2 ቀን 2016 ዓ.ም ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 ቁሊቲ መንደር 4 አካባቢ ይዞ ከሄደ በኋላ ልዑል ጫላ ከተባለው ሌላኛው ግብረ-አበሩ ጋር በመሆን እገታውን መፈጸማቸው ተመላክቷል፡፡

አጋቾቹ ዘግናኝ ምስሎችን ለወላጆቹ በመላክ 10 ሚሊየን ብር እንዲከፍሉ፤ ካልከፈሉ ግን ወጣቱን እንደሚገድሉት የማስፈራሪያ መልዕክት መላካቸውንም ነው ፖሊስ የገለጸው፡፡

የወንጀሉ ሪፖርት የደረሰው የአዲስ አበባ ፖሊስም ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት እና ከፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ ጋር በመሆን ባደረጉት ክትትል ወንጀሉ በተፈፀመ በአራተኛው ቀን ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉ ተጠቅሷል፡፡

ኅብረተሰቡም መሰል ድርጊቶችን ሲመለከት ጥቆማ በመስጠትና ወንጀለኞችን በማጋለጥ በኩል የድርሻውን እንዲወጣ ተጠይቋል፡፡