የሀገር ውስጥ ዜና

በአውሮፓ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ምክክር ተደረገ

By ዮሐንስ ደርበው

December 17, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአውሮፓ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ዛሬ በበይነ መረብ ፍሬያማ ውይይት ማካሄዱ ተገለጸ፡፡

በውይይቱ ላይም÷ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሀገራዊ ምክክሩ ሂደት ውስጥ ሊኖራቸው ስለሚገባ ተሳትፎ እና ድጋፍ ማድረግ በሚችሉባቸው ሁኔታዎች ላይ ምክክር ተደርጓል፡፡

የኮሚሽኑ አባላትም ኮሚሽኑንና የሀገራዊ ምክክር ሂደቱን በተመለከተ ገለፃና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በማብራሪያቸውም÷ ስለ ሀገራዊ ምክክር መሰረታዊ ጽንሰ-ሐሳብ፣ ሀገራዊ ምክክር ለኢትዮጵያ ስላለው ፋይዳ፣ በኮሚሽኑ ስለተከናወኑ ተግባራት እና ኮሚሽኑ የሚገዛባቸውን የሕግ ማዕቀፎች አስረድተዋል፡፡

ማብራሪያና ገለጻውን ተከትሎም በዕለቱ ፍሬያማ ውይይት መደረጉን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

ኮሚሽኑ በአውሮፓ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በትብብር በሚሠራባቸው ሁኔታዎች ላይ ምክረ-ሐሳቦች መቅረባቸውም ተጠቅሷል፡፡

በቀጣይም ኮሚሽኑ መሰል ውይይቶችን በሌሎች የዓለም ክፍሎች ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በማከናወን ለሀገራዊ ምክክሩ ሂደት ግብዓት የሚሆኑ ሐሳቦች መሰብሰቡን እንደሚቀጥል ተጠቁሟል፡፡