አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፍሪካ የአደጋ ስጋት መከላከል አቅም ግንባታ ቡድን ለአደጋዎች ምላሽ በመስጠት በኩል ከኢትዮጵያ ጋር ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን አስታወቀ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በአፍሪካ የአደጋ ስጋት መከላከል አቅም ግንባታ ቡድን ዋና ዳይሬክተር ኢብራሂም ቼክ ዲዮንግ የተመራ የልዑካን ቡድንን ተቀብለው አነጋግረዋል።
በውይይቱ ዋና ዳይሬክተሩ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የአደጋ ስጋት መከላከል ቡድን አባል በመሆኗ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ቡድኑ የኢትዮጵያን ፍላጎት መሰረት በማድረግ ለአደጋዎች ምላሽ ለመስጠት ከሀገሪቱ ጋር ለመስራት ቁርጠኛ ነው ብለዋል፡፡
ቡድኑ በአሁኑ ወቅት 39 አባል ሀገራት እንዳሉት የተጠቀሰ ሲሆን፥ ከእነዚህ ሀገራት ጋር በመተባበርም እንደ ድርቅ፣ ጎርፍ እና ወረርሽኞች ያሉ አደጋዎችን በመቆጣጠር በመላው አህጉሪቱ እንደሚሰራ ጠቅሰዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ፥ ቡድኑ ከኢትዮጵያ አቻው ጋር በመገናኘት የቴክኒክ ቡድንን በመመስረት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ይሰራልም ብለዋል።
በተጨማሪም በቡድኑ እና በኢትዮጵያ መካከል የሚፈረመውን የመግባቢያ ስምምነት እንደሚያዘጋጅም ነው ያነሱት፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በበኩላቸው፥ የዚህ ታዳጊ ኢንሹራንስ ቡድን አባል መሆን ጥሩ አጋጣሚ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ሰው ሰራሽም ይሁን ተፈጥሯዊ አደጋ አንዳንድ ጊዜ የማይቀር ነገር ቢሆንም ጫናውን ለመቀነስ ትንበያ፣ ዝግጁነት እና ምላሽ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሀገራዊ አቅምን በማጎልበት፣ ጠንካራ ምላሽ ሰጪ ዘዴዎችን በመዘርጋት፣ የመልሶ ማቋቋም ስራዎችን በማከናወን አደጋዎችን ለመቋቋም አስፈላጊ እርምጃዎች ናቸውም ብለዋል።
ኢትዮጵያ ይህንን ስትሰራ የቆየችው በብሔራዊ የአደጋ መከላከልና ምላሽ ኮሚሽን አማካኝነት የተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን ያካተተ ሴክሬታሪያት ያለው እንደሆነም ነው የገለጹት አቶ ደመቀ።
ኢትዮጵያ የአደጋ መከላከል ስትራቴጂ ያላት ቢሆንም በግብርና ላይ የበለጠ ትኩረት እንድታገኝ እና ሀገሪቱ አደጋዎችን ለመቋቋም የራሷን አቅም እንድታዳብር እየተከለሰ ነው ማለታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!