የሀገር ውስጥ ዜና

በ2ኛው ምዕራፍ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል – ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)

By Melaku Gedif

December 18, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2ኛው ምዕራፍ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ላይ የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ እድገትን ለማረጋገጥና የዋጋ ንረትን ትርጉም ባለው መልኩ ለመቀነስ ልዩ ትኩረት መሰጠቱን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ገለጹ።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ እና የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈፃፀምን ገምግሟል።

በሪፖርቱ ተቋማዊ የማስፈጸም አቅም፣ የሃብት አጠቃቀም፣ አገልግሎት አሰጣጥ፣ የፖሊሲ ዝግጅት፣ የክትትል እና ግምገማ ስርዓት ውጤታማነትን ለማጎልበት እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ተብራርተዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት የሀገሪቱ ማክሮ ኢኮኖሚ አፈፃጸም ደረጃ እና ለክልሎች የልማት ዕቅድ የሚደረገውን ድጋፍና ክትትል ያለበትን ሁኔታ ጠይቀዋል፡፡

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) በሰጡት ምላሽ÷ መንግስት የ10 ዓመት የልማት ዕቅዱን ለማሳካት ቀጣይነት ያለው ተቋማዊ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በብዝሃ ዘርፍ የዕድገት ምንጮች ባለፉት ሶስት ዓመታት የተከናወኑ ተግባራትን በሚመለከት በተደረገ ግምገማ ውጤት መምጣቱን አብራርተዋል።

ለአብነትም በግብርና ዘርፍ ትኩረት በተሰጣቸው የሰብል፣ የእንስሳት፣ የዓሳ ሃብት ልማት እና የአካባቢና ተፈጥሮ ጥበቃ ስራዎች እድገት ማስመዝገባቸውን ተናግረዋል።

በ2016 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት፣ በወጪ ንግድ እና በሥራ እድል ፈጠራ የተያዘው ዕቅድ አፈጻጸም ላይ ጉድለት እንደታ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ሀገራዊ እና ዓለም አቀፍ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ለዕቅዶች አለመሳካት ምክንያት መሆናቸውን ጠቁመው÷ በቀጣይም ጉድለቶቹን ለማካካስ ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጥ አንስተዋል።

በሁለተኛው ምዕራፍ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ላይ የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ እድገትን ለማረጋገጥና የዋጋ ንረትን ትርጉም ባለው መልኩ ለመቀነስ ልዩ ትኩረት መስጠቱንም ነው ሚኒስትሯ የተናገሩት።

የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ÷ የማክሮ ኢኮኖሚ ስርዓቱን ቀጣይነት ባለው መልኩ በመምራት ሀገራዊ እድገትን ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ለዚህም የተቋማትን የአንድ እቅድ አንድ ሪፖርት የአሰራር ስርዓት በተገቢው መልኩ ተግባራዊ እንዲሆን ጠንካራ የድጋፍና ክትትል ስራ ማከናወን እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ክልሎች በሀገራዊ የልማት ዕቅድ ስኬት አዎንታዊ ሚና እንዲኖራቸው መስራት እንደሚገባም ተናግረዋል።