የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ ለቻይና ገበያ የምታቀርበውን ምርት መጠን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

By Mikias Ayele

December 18, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ወደ ቻይና የምትልከውን የእንስሳትና የግብርና ምርት መጠን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከኢትዮ-ቻይና የወዳጅነት እና የትብብር ኮሚቴ አባላት ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም አምባሳደር ምስጋኑ ÷ ኢትዮጵያ እና ቻይና ያላቸውን ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ  ስልታዊ  ትብብር እና ሁለንተናዊ  ግንኙነት አድንቀዋል።

ነባር ግንኙነቶችን ጨምሮ በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ያለውን ትብብር ትኩረት መስጠት አስፈላጊ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለቻይና ገበያ የምታቀርበውን የግብርና እና የማኑፋክቸሪንግ ምርት ለማሳደግ ፍላጎት እንዳላት ሚኒስትር ዴዔታው ጠቁመዋል።

የኢትዮ-ቻይና የወዳጅነት እና የትብብር ኮሚቴ ሊቀመንበር ዡ ጁንጁን በበኩላቸው÷ ከ10 የቻይና ኩባንያዎች የተወጣጡ 22 የትብብር ኮሚቴ አባላት ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን ገልፀዋል፡፡

የልዑካን ቡድኑ አባላት የኢትዮጵያን የእንስሳትና የግብርና ምርቶች በቻይና ገበያ ለማስተዋወቅ እየሰሩ ነው ማለታቸውንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡