የሀገር ውስጥ ዜና

አይኦኤም ኢትዮጵያ ከስደት ተመላሾችን መልሶ ለማቋቋም የምታደርገውን ጥረት እደግፋለሁ አለ

By Feven Bishaw

December 19, 2023

 

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (አይኦኤም) ኢትዮጵያ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን ለመከላከልና ከስደት ተመላሾችን መልሶ ለማቋቋም የምታደርገውን ጥረት እደግፋለሁ አለ።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ እና የአይኦኤም የኢትዮጵያ ቺፍ ኦፍ ሚሽን አቢባቶው ዋኔ በጋራ መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።

በውይይታቸው መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን ለመከላከል፣ ከስደት ተመላሾችን መልሶ ለማቋቋም እና ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነው ተብሏል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ÷ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን ለመከላከልና ከስደት ተመላሾችን መልሶ ለማቋቋም መንግስት በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ የተለያዩ ፕሮግራሞችን በመቅረፅ ወደ ስራ መገባቱን ገልጸው፤ ይህንን እንቅስቃሴ አይኦኤም እንዲደግፍ ጠይቀዋል።

አቢባቶው ዋኔ በበኩላቸው÷ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን ለመከላከልና ከስደት ተመላሾችን መልሶ ለማቋቋም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ መግለፃቸውን ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ብሎ በለያቸው እና ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራትም ተስማምተዋል።