የሀገር ውስጥ ዜና

በሶማሌ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የሽብር ጥቃት ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 14 የአልሸባብ የሽብር ቡድን አባላት በቁጥጥር ሥር ዋሉ

By ዮሐንስ ደርበው

December 19, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጅግጅጋን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የሽብር ጥቃት ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 14 የአልሸባብ የሽብር ቡድን አባላት በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ- ኃይል አስታውቋል፡፡

አልሸባብ የሽብር ጥቃቶችን እንዲፈጽሙ ስምሪት የሰጠው በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ፣ ፊቅ፣ ዋርዴር እና ቢኬ አካባቢዎች እንደነበርም ነው የተገለጸው፡፡

በጉዳዩ ላይ የጋራ ግብረ ኃይሉ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የላከው መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

በሶማሊ ክልል ጅግጅጋን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የሽብር ጥቃት ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 14 የአልሸባብ የሽብር ቡድን አባላት በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ- ኃይል አስታወቀ፡፡

በሶማሊያ የሰላም ማስከበር ተልዕኮውን በብቃት በመወጣት ላይ በሚገኘው ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ተደጋጋሚ ሽንፈትና ኪሳራ የደረሰበት የአልሸባብ የሽብር ቡድን አባላትን በህቡእ በመመልመልና በማደራጀት በሶማሌ ክልል በጅግጅጋ ከተማ እና በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የሽብር ጥቃት በመፈፀም ከፍተኛ ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳቶችን ለማድረስ ዕቅድ አውጥቶ ለመንቀሳቀስ ቢሞክርም ሴራው ሙሉ በሙሉ መክሸፉን የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ- ኃይል ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መግለጫ አስታውቋል።

አልሸባብ በህቡዕ አደራጅቶና ተልዕኮ ሰጥቶ የላካቸው 14 የቡድኑ አባላት ሊጠቀሙባቸው ካዘጋጇቸው ተቀጣጣይ ቁሶችና የተለያዩ ሰነዶች ጋር በቁጥጥር ስር የዋሉት በኢትዮጵያና በሶማሊያ ድንበር ሾልከው ወደ ሶማሌ ክልል ዘልቀው በመግባት በጅግጅጋና በሌሎችም የክልሉ ከተሞችና አካባቢዎች ኢላማዎችን በመለየት የሽብር ጥቃት ለመፈፀም ዕቅድ አውጥተው ሲንቀሳቀሱ መሆኑን መግለጫው ጠቁሟል።

በህግ ቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ከተደረጉት ከእነዚህ ተጠርጣሪዎች መካከል አሊ አብዲ በቅፅል ስሙ መዓሊን አሊ በመባል የሚታወቀው የሽብር ቡድኑ መሪና አስተባባሪ መቀመጫውን ሶማሊያ ካደረገው የአልሸባብ ክንፍ ጋር ግንኙነት በመፍጠር በሶማሌ ክልል ውስጥ ሆኖ የሽብር ቡድን አባላትን በማደራጀት፣ በመገናኛት፣ በመመልመል፣ የሽብር እቅድ በማውጣትና ኢላማዎችን በመለየት ጥቃቶች እንዲፈፅሙ የሥልጠናና የሎጀስቲክስ ድጋፎችን ሲያደርግ ከሌሎች 13 ግብረ አበሮቹ ጋር በተካሄደው የተቀናጀ ክትትል በሞያሌ ከተማ የመግቢያ ኬላ በኩል ሾልኮ ለመውጣት ሲሞክር በቁጥጥር ሥር መዋሉን የጋራ ግብረ- ኃይሉ መግለጫ አመልክቷል፡፡

አልሸባብ የሽብር ጥቃቶችን እንዲፈጽሙ ስምሪት የሰጠው በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ፣ ፊቅ፣ ዋርዴር እና ቢኬ አካባቢዎች እንደነበር ያመለከተው መግለጫው÷ የህቡዕ አደረጃጀት በመፍጠር የሽብር ተልዕኮ ለመፈጸም የተንቀሳቀሱት ተጠርጣሪዎች ለሽብር ጥቃቶች ሊጠቀሙባቸው ካዘጋጇቸው በርካታ ክላሽንኮቭ መሳሪያዎች፣ ጥይቶች፣ ሽጉጦች፣ ቦንቦች፣ ተቀጣጣይ ቁሶችና የተለያዩ ሰነዶች ጋር መያዛቸውን አስታውቋል፡፡

በተጨማሪም የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ- ኃይሉ በሶማሌ ክልል በሲቲ ዞን ምኤሶ ወረዳ፣ ፋፋን ዞን ጅግጅጋ ከተማና ዙሪያው፣ ዶሎ ዞን ዋርደር ከተማና ዙሪያው፣ ቆራሄ ዞን ህግሎሌ ወረዳ እና ኤረር ዞን ፊቅ ከተማ ባካሄደው ተከታታይ ኦፕሬሽኖችና የአሰሳ ሥራዎች የሽብር ቡድኑ ለጥቃት ሊያውሏቸው የነበሩ 84 ክላሽንኮቭ መሣሪያዎች፣ 10 የቡድን መሣሪያዎችና 12 ሽጉጦች በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ መደረጉን መግለጫው አክሎ ገልጿል።

በተለይም አልሸባብ በኢትዮጵያ ላይ ዒላማ ያደረገውን የሽብር እኩይ ሴራና ጥቃት ለማሳካት የፈንጅ መቀመሚያ ንጥረ ነገሮች በህቡዕ ባደራጃቸው ህዋሶች አማካኝነት በህገ ወጥ መንገድ በኢትዮጵያ ድንበር ወደ ደቡብ ሶማሊያ በሟጓጓዝ ላይ እያለ በኤረር ዞን ጋሻሞ ወረዳ በቁጥጥር ሥር እንዲውል መደረጉን የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ- ኃይል ባወጣው መግለጫ አያይዞ ጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ከሶማሊያና ሌሎች አጎራባች ክልሎች ጋር ሰፊ ድንበር የሚጋራ በመሆኑ የአልሻባብ የሽብር ቡድን ሃሰተኛ መታወቂያዎችና ፓስፖርቶችን እንዲሁም ሌሎች ሰነዶችን በመጠቀም አባላቶቹን ወደ ኢትዮጵያ አስርጎ በመስገባት በመሠረተ ልማቶችና የነዳጅ ማጠራቀሚያዎች ላይ የሽብር ጥቃቶችን ለመፈጸም ተደጋጋሚ ጥረቶችን ሲያደረግ ቆይቷል ያለው መግለጫው ፤ ከውጭ አቻ የመረጃ ተቋማት ጋር በሚደረግ የመረጃ ልውውጥ እንዲሁም እየተካሄዱ ባሉ ጥብቅ ክትትሎችና ኦፕሬሽኖች አማካኝነት የሽብር ሴራዎችንና ተልዕኮዎችን ማክሸፍ መቻሉን የጋራ ግብረ- ኃይሉ ጠቁሟል።

በዚህ አጋጣሚ የሽብር ቡድኑ ሴራዎች እንዲከሽፉ፤ የሶማሌ ክልል መንግስት የፀጥታ መዋቅር እና የክልሉ ህዝብ ላደረገው ከፍተኛ አስተዋፅኦ የጋራ ግብረ- ኃይሉ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡

በመጨረሻም በመላ ሀገሪቱ የፀጥታና ደኅንነት ስጋቶችን በማስወገድና በሽብር ቡድኖች እንዲሁም በፀረ-ሰላም ሀይሎች የሚታቀዱ የጥፋት ሴራዎችን በማክሸፍ እና በቁጥጥር ስር እንዲውሉ በማድረግ በኩል የብሄራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እና የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በመቀናጀት እየወሰዱት ያለው እርምጃ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ- ኃይል ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መግለጫ አረጋግጧል፡፡ የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ- ኃይል ታህሳስ 9/2016 ዓ.ም