የሀገር ውስጥ ዜና

በጅቡቲ ፓርላማ አፈ-ጉባዔ የተመራ ልዑክ በኢትዮጵያ ጉብኝት እያደረገ ነው

By ዮሐንስ ደርበው

December 20, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጅቡቲ ፓርላማ አፈ-ጉባዔ ዲሌታ መሐመድ የተመራ የልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት እያደረገ ነው፡፡

ልዑኩ ትናንት ማምሻውን አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ÷ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎና ሌሎች የምክር ቤቱ አመራሮች አቀባበል አድርገውለታል።

ልዑካን ቡድኑ በአሁኑ ወቅት ከአፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎና ሌሎች የምክር ቤቱ አመራሮች ጋር የሁለትዮሽ ውይይት በማካሄድ ላይ ይገኛል።

ወደ ኢትዮጵያ የመጣው የጅቡቲ ፓርላማ ልዑክ ከአፈ ጉባዔ ዲሌታ በተጨማሪ የኢትዮ-ጅቡቲ የወዳጅነት ቡድን ሊቀ-መንበር እና ምክትል ሊቀ-መንበር እንዲሁም የፓርላማ አባላትን ያካተተ መሆኑ ታውቋል።

በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብርሀኑ ጸጋዬ እንደገለጹት÷ የጅቡቲ ፓርላማ ከፍተኛ አመራሮች ጉብኝት የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ትልቅ አስተዋጽኦ አለው።

በሀገራቱ መካከል ያለውን ጠንካራ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የሕዝብ ለሕዝብ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ምዕራፍ ለማሸጋገርም ሚናው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

የልዑካን ቡድኑ በኢትዮጵያ ለሦስት ቀናት በሚያደርገው ቆይታ የልማት ሥራዎችን የሚጎበኝ ሲሆን÷ የልምድ ልውውጥ መድረኮች እንደሚኖሩት መጠቀሱን ኢዜአ ዘግቧል።

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!