የሀገር ውስጥ ዜና

አካታች የምክክር ሂደት እንዲኖር የተሳታፊዎች ልየታ መከናወኑ ተገለጸ

By ዮሐንስ ደርበው

December 20, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አካታችና አሳታፊ የምክክር ሂደት እንዲኖር የተሳታፊዎች ልየታ ሥራ በክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች መከናወኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የኢትዮጵያ የሐይማኖት ተቋማት ጉባዔ፣ ዕድሮች፣ የጋራ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤትን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተባባሪነት እንዲሳተፉና ኮሚሽኑን እንዲያግዙ በማድረግ ረገድ የተሻለ ሥራ መሠራቱ ተገልጿል፡፡

በተከናወኑት ተግባራትም የሀገራዊ ምክክር ዓላማና ሂደቱን ሕብረተሰቡ እንዲገነዘብ ከሚከናወነው ሥራ ጎን ለጎን የምክክር ሂደቱ አካታችና አሳታፊ እንዲሆን በትብብር እየተሠራ መሆኑን የኮሚሽኑ ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም ተናግረዋል፡፡

እስካሁንም ለተባባሪ አካላት በሀገራዊ ምክክር ዓላማና የተሳታፊዎች ልየታ ሥነ-ዘዴ ላይ ስልጠና መሰጠቱን ጠቅሰው÷ በዚህም በሐረሪ፣ ሲዳማ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ቤኒሻንጉል ጉምዝና ጋምቤላ ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደሮች የተሳታፊዎች ልየታ መከናወኑን አመላክተዋል፡፡

በተመሳሳይ በአፋርና ሶማሌ ክልል የተሳታፊዎች ልየታ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው÷ በደቡብና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ደግሞ የተባባሪ አካላት ስልጠና በመስጠት የተሳታፊዎች ልየታ ለማከናወን በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል የተሳታፊዎች ልየታ ለማከናወን ለ2 ሺህ 500 ተባባሪ አካላት ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ገልጸው÷ ከክልሉ 8 ዞኖችና ከሸገር ከተማ አስተዳደር ለተውጣጡ ተባባሪ አካላት በመጀመሪያው ዙር ስልጠና ተሰጥቷል ብለዋል፡፡

በክልሉ የተባባሪ አካላት ስልጠና እንደተጠናቀቀም በቀጣይ የተሳታፊዎች ልየታ እንደሚከናወን ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡

በእስከአሁኑ ሂደትም በተሳታፊዎች ልየታ ከ70 ሺህ በላይ የሕብረተሰብ ክፍሎች መሳተፋቸውን አንስተዋል።

በአማራና ትግራይ ክልሎችም የተባባሪ አካላትና ተሳታፊዎች ልየታ በቀጣይ የሚከናወን መሆኑንም አመላክተዋል፡፡