የሀገር ውስጥ ዜና

በኢትዮጵያ ከእንሰት ተረፈ ምርት ወረቀት ማምረት ተጀመረ

By ዮሐንስ ደርበው

December 20, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ከእንሰት ተረፈ ምርት ወረቀት ማምረት መጀመሩን አዳል ኢንዱስትሪ አስታወቀ፡፡

ከእንሰት ተረፈ ምርት ወረቀቶችን በማምረት የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ለማሟላትና ለወረቀት ግዥ የሚወጣውን የውጪ ምንዛሪ ለማስቀረት እየሠራ መሆኑንም ነው ኢንዱስትሪው የገለጸው፡፡

ኢንዱስትሪው ባቋቋመው ፋብሪካ ከአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በተደረገለት ሙያዊ ድጋፍ ከእንሰት ተረፈ ምርት ወረቀት ማምረት መጀመሩን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በኢትዮጵያ የእንሰት ምርት ከምግብነቱ ባሻገር ተረፈ-ምርቱ ለመድኃኒት፣ ለእንስሳት መኖ እንዲሁም ለወረቀት ማምረቻና ሌሎች አገልግሎቶች እንደሚውልም ነው የተብራራው፡፡

በአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የምርምርና ቴክኖሎጂ ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዴሲሳ ያደታ (ዶ/ር) እንደዳሉት÷ በእንሰት ተክል ላይ በተደረገ ጥናት ለወረቀት ማምረቻ ግብዓትነት እንደሚውል ተረጋግጧል።

በምርምሩን ውጤት መሰረትም አዳል ኢንዱስትሪ የተሰኘ አምራች ኩባንያ ከኢንስቲትዩቱ ጋር በመተባበር በይፋ ወረቅት ማምረት መጀመሩን ነው ያስታወቁት፡፡

ኢትዮጵያ ለወረቅት ግዢ በየዓመቱ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ እንደምታደርግ ጠቁመው÷ ወደ ምርት የገባው ኢንዱስትሪ የሀገር ውስጥ ፍላጎትን በተኪ ምርት ለማሟላት እንዲሠራ ጠይቀዋል፡፡

አሁን የተጀመረውን የማምረት ሂደትም ሌሎች ፋብሪካዎች እንዲሰማሩበት ይደረጋል ነው ያሉት፡፡

የአዳል ኢንዱስትሪ ሥራ አስኪያጅ አዳነ በርሄ በበኩላቸው÷ ፋብሪካው ለጋዜጣ፣ ለመጽሐፍ፣ ለካርቶንና ለመጠቅለያ የሚሆን ወረቀት ማምረት መጀመሩን ጠቅሰዋል፡፡

ለወረቀት ምርቱ ግብዓት ሆኖ የሚያገለግለውን ተረፈ ምርት በዘላቂነት ለማግኘት በሀገሪቱ እንሰት አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች ከሚኖሩ አርሶ አደሮች ጋር ትስስር በመፍጠር ላይ መሆናቸውንም ነው ያስረዱት፡፡

ኢንዱስትሪው በአማካይ በዓመት 30 ሺህ ቶን ወረቀት የማምረት ዐቅም እንዳለው ጠቅሰው÷ በቀጣይ ይህን በማሳደግ የሀገር ውስጥ ፍጆታን ከማሟላት ባሻገር ምርቱን ወደ ውጪ የመላክ ዕቅድ ሰንቆ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!