አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በትምህርት መስክ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያደርገውን ትብብር አጠናክሮ መቀጠል እንደሚፈልግ የሩሲያ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የትምህር ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ከሩሲያ ትምህርት ሚኒስቴር እንዲሁም የሩሲያ የትምህርትና ምርምር ተቋማት ከተውጣጡ የልዑካን ቡድን አባላት ጋር ተወያይዋል፡፡
በውይይታቸውም÷ በኢትዮጵያ እና ሩሲያ መካከል ባለው የትምህርትና ሥልጠና ትብብር ላይ መክረዋል፡፡
አሁን ላይ በኢትዮጵያ ተግባራዊ እየሆነ ያለውን የትምህርት ሥርዓት፣ መዋቅር እና ስትራቴጂካዊ የትኩረት አቅጣጫዎች ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡
የትምህርት ጥራትን ጨምሮ በመጪዎቹ ዓመታት የትምህርት ዘርፉን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ እየተከናወኑ ያሉ የሪፎርም ሥራዎችን አብራርተዋል።
የሩሲያ ትምህርት ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ ትብብር እና ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኡስማን አብዱልአዝቪክ በበኩላቸው÷ ሩሲያ ከኢትዮጵ ጋር ያላትን የትምህርትና ስልጠና ትብብር ከፍ ወዳለ ደረጃ የማድረስ ፍላጎት እንዳላት አረጋግጠዋል፡፡
አሁን ላይ በሀገራቱ መካከል በትግበራ ላይ ያለውን የትምህርትና ሥልጠና የመግባቢያ ስምምነት ማሻሻልና ማደስ ይገባል ማለታቸውን የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡
በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለውን የትምህርት ትብብር ለማደስ የሚከናወኑ ቀሪ ስራዎች በዲፕሎማቲክ ቻናል በኩል ለመፈጸም ሁለቱ ወገኖች ከስምምነት ደርሰዋል፡፡
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!