አዲስ አበባ ፣ ታኅሣስ 10 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረሪ ክልል ባለፉት ዓመታት ለኢንተርፕራይዞች በብድር የተሰጠውን ገንዘብ በአግባቡ ለማስመለስ ባለድርሻ አካላት በትኩረት እንዲሰሩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ አሳሳቡ።
በክልሉ ለኢንተርፕራይዞች የተሰጠውን ብድር የሚያስመልስ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ ዛሬ ወደ ሥራ የገባ ሲሆን የቀጣይ አቅጣጫም ተቀምጧል።
የሐረር ብድርና ቁጠባ ተቋም ባቀረበው ሪፖርት እንደተመለከተው፥ ባለፉት ዓመታት በክልሉ በመደበኛ እና በተዘዋዋሪ ፈንድ እስከ 300 ሚሊየን ብር ለኢንተርፕራይዞች በብድር የተሰጠ ቢሆንም ከዚህ ውስጥ የተመለሰው በጣም ዝቅተኛ ገንዘብ ነው።
ለኢንተርፕራይዞች በብድር የተሰጠው ገንዘብ ያልተመለሰበት ዋነኛ ምክንያት የአመራሩ ቁርጠኝነት አናሳ መሆንና ቅንጅታዊ አሰራር አለመኖሩ መሆኑ በውይይቱ ወቅት ተገልጿል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ለኢንተርፕራይዞች የተሰጠውን ብድር ለማስመለስ የክልሉ ብድርና ቁጠባ ተቋም ብቻውን በቂ ባለመሆኑ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባት አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸዋል።
“በብድር የተሰጠው ገንዘብ ተሰባስቦ ለሌሎች ኢንተርፕራይዞች የብድር አገልግሎት እንዲውል አመራሩ የተሰጠውን ሃላፊነት በአግባቡ መወጣት ይኖርበታል” ሲሉም አመላክተዋል። የተቋቋመው ግብረ ሃይል ከወገንተኝነት በጸዳ መልኩ ሃላፊነቱን በመወጣት ብድር የማስመለስ ስራውን ውጤታማ ማድረግ አለበት ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በብድር የተሰራጨው ገንዘብ ተመልሶ ለሌሎች ብድር ፈላጊዎች እንዲውል ለሚሰራው ሥራ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አቶ ኦርዲን አረጋግጠዋል።
ብድሩን ለማስመለስ በተቋቋመው ግብረሀይል የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ፣ የሰላምና ፀጥታ ጉዳይ አስተዳደር፣ ኢንተርፕራይዝ ኢንዱስትሪ ቢሮዎች እና የክልሉ ብድርና ቁጠባ ተቋም መካተታቸው ታውቋል።