አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት መንግስታት የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ ፈንድ (ዩኤንሲኢአርኤፍ) በኢትዮጵያ ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች የሚውል 23 ሚሊየን ዶላር መመደቡን አስታወቀ፡፡
የአደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን እና አጋር ድርጅቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ አደጋዎች የተጠቁ አካባቢዎች ያለውን የሰብዓዊ ድጋፍ ክፍተት መሙላት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል፡፡
በውይይቱ ችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች ድጋፍ ለማድረግ ያላቸውን ትብብርና ለማጠናከር መስማማታቸውን የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡
በተመድ የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ ፈንድም በጎርፍ አደጋ ለተጎዱት 8 ሚሊየን ዶላር፣ በወረርሽኝ ለተጠቁ 5 ሚሊየን ዶላር እንዲሁም በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ደግሞ 10 ሚሊየን ዶላር በአጠቃላይ 23 ሚሊየን ዶላር መመደቡን በመድረኩ አስታውቋል፡፡
የዓለም ምግብ ፕሮግራም እና ክሪስቲያን ሪሊፍ ሰርቪስ በበኩላቸው÷ በአማራ፣ ትግራይና አፋር ክልሎች የሰብዓዊ ድጋፍ ለማዳረስ የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ቃል ገብተዋል፡፡
የሰብዓዊ ድጋፍ ተጠቃሚዎችን ለመለየት የዲጂታል መታወቂያን በመጠቀም ድጋፍን ለማዳረስ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይም ምክክር ተደርጓል፡፡
የአራት ወራት የአፋጣኝ ጊዜ ምላሽ ዕቅድ ትግበራ ላይም ባለድርሻ አካላት እንዲረባረቡ ጥሪ ቀርቧል፡፡
ሰብዓዊ ድጋፍ አቅራቢዎች ተረጂዎችን በቤተሰብ ደረጃ ለመለየት የሚያስችል የተናበበ የአሰራር ስርዓትን ለመተግበር በምክክሩ ወቅት መስማማታቸው ተጠቁሟል፡፡
በውይይት መድረኩ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተ/ማሪያም (ዶ/ር) እና በተመድ የኢትዮጵያ ዋና ተጠሪ ራሚዝ አላክባሮቭ (ዶ/ር) የተመራ የአጋር ድርጅቶች አመራሮች ልዑካን ተሳትፈዋል፡፡