የሀገር ውስጥ ዜና

የከተራና ጥምቀት በዓል የመቻቻልና የአብሮነት እሴትን ጠብቀው እንዲከበሩ ዝግጅት ተጀምሯል

By Shambel Mihret

December 21, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የ2016 ዓ.ም የከተራና ጥምቀት በዓል የመቻቻልና የአብሮነት እሴትን ጠብቀው እንዲከበሩ ከወዲሁ ዝግጅት ተጀምሯል።

የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ እና የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሥራ ኃላፊዎች ጋር ምክክር አካሂደዋል።

የከተማዋ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ምክትል ኃላፊ ፍቅሬ ግዛው÷ የዘንድሮው የከተራና ጥምቀት በዓል በመቻቻልና በአብሮነት እሴትን ጠብቀው እንዲከበሩ ቢሮው አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረገ ነው ብለዋል።

ከፀጥታ አካላትና ከነዋሪዎች ጋር በመቀናጀት በዓሉ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከናወን ቢሮው የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የሐይማኖት አባቶችም ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት በመሆኑ ከወዲሁ ትኩረት በመስጠት መሥራት እንዳለባቸው አመላክተዋል፡፡

የአዲስ አበባ የሐይማኖት ተቋማት ጉባዔ ሰብሳቢ መጋቢ ታምራት አበጋዝ በበኩላቸው÷ የከተራና ጥምቀት በዓል በደማቅ ሐይማኖታዊ ሥርዓት ከኢትዮጵያውያን አልፎ የውጭ ሀገር ዜጎች በመታደም የሚያከብሩት ነው።

በዓሉ የኢትዮጵያውያንን ማህበራዊ ትስስር፣ ወንድማማችነትና አብሮነትን በማጠናከር በኩልም ሚናው የጎላ ነው ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

የከተማዋ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ እና የአዲስ አበባ ሐይማኖት ተቋማት ጉባዔ በዓሉ በሰላም እንዲከበር እያደረጉት ላለው ቅድመ ዝግጅትም አመስግነዋል፡፡