የሀገር ውስጥ ዜና

የኮንዶሚኒዬም በር ገንጥሎ በመስረቅና ግለሰብ ደብድቦ በመዝረፍ የወንጀል ድርጊት የተከሰሱ በእስራት ተቀጡ

By Feven Bishaw

December 22, 2023

 

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኮንዶሚኒዬም በር ገንጥሎ በመስረቅና ግለሰብ ደብድቦ ንብረት በመዝረፍ የወንጀል ድርጊት የተከሰሱ እስከ አምስት አመት በሚደርስ እስራት እንዲቀጡ የሸገር ከተማ የኮዬ ፌጬ ወረዳ ፍርድ ቤት ውሳኔ አሳለፈ።

የቅጣት ውሳኔ የተወሰነባቸው ተረፈ ቦኪና፣ አንጋሳ ደበላና አዳነ ሆስቴ የተባሉ ግለሰቦች ናቸው።

የኮዬ ፌጬ ክ/ከተማ ምድብ ዐቃቤ ሕግ መዝገቦችን አደራጅቶ ተረፈ ቦኪና እና ታደሰ አንጋሳ በተባሉ ተከሳሾች ላይ ሁለት የወንጀል ክስ አቅርቦባቸዋል።

በክሱ ላይ እንደተመላከተው ተከሳሾቹ ካልተያዘ ግብረአበራቸው ጋር በመሆን በመስከረም 2 ቀን 2016 ዓ.ም ከምሽቱ 2:00 ሰዓት ላይ በኮዬ ፌጬ ጀነራል ታደሰ ብሩ ት/ቤት አካባቢ ጨለማን ተገን በማድረግ አስቻለው ጌታሁን የተባለ ግለሰብን ከኋላ በድንጋይ ጭንቅላቱን በመምታት መሬት ላይ በመጣልና እንዳይጮህ አፉን በማፈን ይዞት የነበረውን ጥሬ 10 ሺህ እና የሞባይል ስልክ በመስረቅ ሊሰወሩ ሲሉ በአካባቢው ነዋሪዎች ደርሰው በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉ በክሱ ተጠቅሷል።

የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1 ሀ እና አንቀጽ 556 ንዑስ ቁጥር 2 ሀ እንዲሁም በአንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1 እና በአንቀጽ 670 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ ተላልፈዋል በማለት ቀላል የአካል ጉዳት ማድረስና የውንብድና ወንጀል ክስ አቅርቦባቸዋል።

ሌላኛው አዳነ ሆስቴ የተባለ ተከሳሽን በሚመለከት ደግሞ በመስከረም 17 ቀን 2016 ዓ.ም ምሽት 1:00 ሰዓት ላይ ተገቢ ያልሆነ ብልጽግና ለማግኘት በማሰብ በኮዬ ፌጬ ኮንዶሚኒዬም ብሎክ 7 ላይ የሚገኝ የግለሰብ የኮንዶሚኒዬም የመኖሪያ ቤት የብረት በር ገንጥሎ ሰርቆ የወሰደ መሆኑ በክሱ ተጠቅሶ የወንጀል ህግ አንቀጽ 669 ንዑስ ቁጥር 3 ለ ስር የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ ከባድ ስርቆት ወንጀል ተከሷል።

ተከሳሾቹ በተለያዩ መዝገቦች የቀረበባቸው ክስ በችሎት ከደረሳቸውና በንባብ ከተሰማ በኋላ በክስ ዝርዝሩ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸማቸውን ገልጸው የዕምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል።

ዐቃቤ ሕግም ለወንጀሉ መፈጸም ያስረዳሉ ያላቸውን አራት ምስክሮችን ቃል በማሰማት የሰነድ ማስረጃዎችንም አቅርቧል።

ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ሕግን ማስረጃ መርምሮ ሁሉንም ተከሳሾች በተከሰሱበት ድንጋጌ እንዲከላከሉ ብይን የሰጠ ቢሆንም ተከሳሾቹ ግን የዐቃቤ ሕግን ማስረጃ በተገቢው ማስተባበል ባለመቻላቸው የጥፋተኝነት ፍርድ ተሰጥቶባቸዋል።

ከዚህም በኋላ ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየቶችን በመያዝ ተረፈ ቦኪ እና አንጋሳ ደበላ የተባሉ ተከሳሾች እያንዳንዳቸውን በ3 አመት ከ3 ወራት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል።

ሌላኛው አዳነ ሆስቴ የተባለውን ተከሳሽ በሚመለከት ደግሞ በ5 አመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል።

በታሪክ አዱኛ