የሀገር ውስጥ ዜና

በመዲናዋ ፖሊስ ባካሄደው የተቀናጀ ኦፕሬሽን በርካታ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

By Feven Bishaw

December 22, 2023

 

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እና የአዲስ አበባ ፖሊስ በአዲስ አበባ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ባካሄዱት የአምስት ቀናት የተቀናጀ ኦፕሬሽን ከ1 ሺህ በላይ ተጠርጣሪዎችን ከበርካታ ልዩ ልዩ ማስረጃዎች ጋር በቁጥጥር ስር ማዋላቸው ተገለፀ፡፡

በዚሁ መሰረት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስና የአዲስ አበባ ፖሊስ በአዲስ አበባ ከተማ ህብረተሰቡን ሲያማርሩ የቆዩ የወንጀል ተግባራትን ለመከላከል ያካሄዱትን ኦፕሬሽን በጋራ በመገምገም ዛሬ በሰጡት መግለጫ ከ1ሺህ በላይ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውን አንስተዋል።

በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ተጠርጣሪዎችም አራት ሽጉጦች፣ 68 የሽጉጥ ጥይት፣ አምስት ልዩ ልዩ መኪኖች፣ 64 የተሽከርካሪ ሰሌዳዎች፣ 1 ሺህ 461 ልዩ ልዩ የተሽከርካሪ ዕቃዎች፣ ሶስት ባጃጅ፣ አንድ ጀኔሬተር፣ 290 ሞተር ሳይክሎች፣ ስምንት ፔዳል ብስክሌት፣ 31 ሺህ የአሜሪካ ዶላር፣ 1ሺህ 578 ልዩ ልዩ የሞባይል ስልኮች፣ 52 ታብሌት፣ 71 ላፕቶፕ፣ 12 ኤሌክትሪክ መቆጣጠሪያ ስታብላይዘር ተይዟል ተብሏል፡፡

እንዲሁም 58 ልዩ ልዩ የዲሽ ዕቃዎች፣ 48 ቴሌቪዥን፣ 44 ሲምካርድ፣ 10 የመንገድ ፍሳሽ ማስወገጃ የብረት ክዳን፣ ሁለት ግራይንደር፣ ከ5 ኪሎ ግራም በላይ ካናቢስ አደንዛዥ ዕፅ፣ 1 ሺህ 292 የሺሻ ማስጨሻ ዕቃዎች እና 153 ልዩ ልዩ አልባሳት እንዲሁም በግለሰብ ቤት ተከማችቶ የነበረ ለግብይት የሚያገለግል 90 ከረጢት የኢትዮጵያ ሳንቲሞች በማስረጃነት መያዙም ነው የተገለጸው።

በኦፕሬሽኑ 37 ቁማር ቤቶች እና 3 ሺህ 241 የቤቲንግ ቤቶች መታሸጋቸውን የገለፀው መግለጫው በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በቤት ውስጥ ጥይቶችን የሚያመርት አንድ ተጠርጣሪን ከ4 ሺህ 52 የክላሽ ጥይት፣ 1 ሺህ 297 ባዶ የክላሽ እርሳስ እና 1 ሺህ 319 የክላሽ ቀለሀ እንዲሁም ከሚያመርትበት ማሽኖች ጋር በቁጥጥር ስር መዋሉን ሁለቱ የፖሊስ ተቋማት በሰጡት መግለጫ አረጋግጠዋል።

የሀገር ኢኮኖሚን ለማዳከም የተለያዩ ሀገራት ሀሰተኛ ገንዘቦችን የሚያትሙ እና በጥቁር ገበያ የሚመነዝሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋሉን ከፌደራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ህብረተሰቡ ሰነድ አልባ የሆኑ ዕቃዎችን ከመግዛት እንዲቆጠብ እና የሚያደርገውን ግብይት በህጋዊ ሰነድ እና ህጋዊ ደረሰኝ ብቻ እንድያደርግ በመግለጫቸው አሳስበዋል።

መግለጫው አያይዞ እነዚህ ወንጀሎች ለኅብረተሰቡ የፀጥታ ሥጋት ከማይሆኑበት ደረጃ ላይ ለማድረስ ተከታታይ የተቀናጀ ኦፕሬሽን አጠናክሮ በመቀጠል የወንጀል ፈፃሚዎችን እና የሌባ ተቀባዮችን ሰንሰለት የመበጣጠስ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተገልጿል፡፡

በቀጣይ ለሚካሄደው ኦፕሬሽን የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ለፖሊስ መረጃ በመስጠት የተለመደ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ ቀርቧል።