የሀገር ውስጥ ዜና

ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር) በውጭ ሀገራት የተወለዱ ሁለተኛው ትውልድ የዳያስፖራ አባላት ወደ ሀገራቸው እንዲመጡ ጥሪ አቀረቡ

By ዮሐንስ ደርበው

December 23, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በውጭ ሀገራት የተወለዱ ሁለተኛው ትውልድ የዳያስፖራ አባላት ወደ ሀገራቸው እንዲመጡ ጥሪ አቀረቡ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪውን ያቀረቡት የገበታ ለሀገር ኮይሻ ፕሮጀክት አካል የሆነውን የጨበራ ዝሆን ዳና ሎጅን መርቀው በከፈቱበት ወቅት ነው።

በዚህም በውጭ ሀገራት የተወለዱ ሁለተኛው ትውልድ የዳያስፖራ አባላት ከታኅሣስ 20 ቀን 2016 እስከ መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም በሦስት ዙር ወደ ሀገራቸው እንዲመጡ ጠይቀዋል።

በዚሁ መሠረት የመጀመሪያው ዙር ከታኅሣስ 20 እስከ ጥር 20 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ ሲሆን “connect to your culture” በሚል ሐሳብ የተደረገ ጥሪ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ወደ ሀገር ቤት የሚመጡ የዳያስፖራ አባላትም የገና ዓልን ጨምሮ በሌሎች በዓላት ላይ እንደሚታደሙ አስታውቀዋል፡፡

ሁለተኛው ዙር ደግሞ “connect to your history” በሚል መሪ ሐሳብ በአዲስ አበባ በሚካሄደው የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ወቅት እንዲመጡ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።

እንዲሁም ሦስተኛው ዙር “live your legacy” በሚል መሪ ሐሳብ በኢትዮጵያ ከክረምት ወቅት ጀምሮ እስከ መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚካሄድ ተናግረዋል።

በዚሁ ጊዜ የሚመጡ የዳያስፖራ አባላትም ችግኝ መትከልን ጨምሮ በሌሎች ሥራዎች እንደሚሳተፉ ጠቅሰዋል፡፡

ወደ ሀገር ቤት ለሚመጡ የዳያስፖራ አባላት በኢትዮጵያ ዓየር መንገድና በኢትዮጵያ ሆቴሎች ልዩ የቅናሽ ክፍያ አገልግሎት እንደሚኖርም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ያስታወቁት፡፡

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!