የሀገር ውስጥ ዜና

 የአማራ ክልል ምክር ቤት የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት የመሬት ካሳ ውሳኔ ሀሳብን መርምሮ አፀደቀ

By Mikias Ayele

December 23, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት የመሬት ካሳ ውሳኔ ሀሳብን መርምሮ አፀደቀ፡፡

በደቡብ ወሎ ዞን ተሁለደሪ ወረዳ የሚገኘው የሎጎ ሐይቅ በጠቅላይ ሚኒስትር  ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)በገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት አማካኝነት ለማልማት የተመረጠ መሆኑ ይታወቃል።

ሐይቁ በገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት ለመልማት በመመረጡ በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ እጅግ ከፍተኛ ደስታን ፈጥሯል።

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት መስተዳድር ምክር ቤትም በገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት የተመረጠውን የሎጎ ሐይቅ ከሶስተኛ ወገን ነጻ ለማድረግ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ መርምሮ ውሳኔ ማሳለፉን ከአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በዚህ መሠረት የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት በዛሬው እለት ባካሄደው ጉባኤ ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልገውን የካሣ ክፍያ በጀት በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።