የሀገር ውስጥ ዜና

ጥቁር አንበሳ የአየር ትርዒት የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የአየር ትርዒት ብራንድ ሆኖ ይቀጥላል – ሌ/ጄ ይልማ መርዳሳ

By Shambel Mihret

December 24, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 88ኛው የአየር ኃይል የምስረታ ቀን የበዓል አከባበር ላይ “ጥቁር አንበሳ” በሚል የተካሄደው የአየር ትርዒት የኢትዮጵያ አየር ኃይል አለም አቀፍ የአየር ትርዒት ብራንድ ሆኖ እንደሚቀጥል የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ገለፁ።

88ኛው የአየር ኃይል ቀን የበዓል አከባበር በታላቅ ድምቀት መጠናቀቁን ተከትሎ ልዩ የምስጋናና የእውቅና ፕሮግራም ተካሂዷል።

በመርሐ ግብሩ ላይ ሌ/ጄ ይልማ መርዳሳ÷ 88ኛው የምስረታ በዓል አከባበር በታሪካዊው የጥቁር አንበሳ የዓለም አቀፍ የአየር ትርዒት እና በአፍሪካ የመጀመሪያው የአየር ኃይል ፎረምን ጨምሮ በሌሎችም ዝግጅቶች በስኬት መጠናቀቁን ገልፀዋል፡፡

ይህ ስኬት መላው የተቋሙ አባላት እጅ ለእጅ ተያይዘው በጋራ በመስራታቸው የተገኘ ውጤት በመሆኑ ሁሉም ምስጋናና ክብር ይገባቸዋል ብለዋል።

የቀረበው የአየር ትርዒት ዓለም የተደመመበትና አብራሪዎቻችንም በየትኛውም ዓለም አቀፍ የአየር ትርዒት ላይ መሳተፍ የሚያስችል አቅም እንዳላቸው በተግባር ያረጋገጡበት ነበር ሲሉ ገልጸዋል፡፡

“ጥቁር አንበሳ” የሚለው የአየር ትርዒት ከእንግዲህ ማንም መቀማት የማይችለውና የኢትዮጵያ አየር ኃይል ብቻ የሆነ ዓለም አቀፍ የአየር ትርዒት ብራንድም ሆኖ ይቀጥላል ብለዋል።

በዕለቱ ለአጋር ተቋማትና ድርጅቶች የተሻለ ውጤት ላሳዩ የስራ ክፍሎችና የጎላ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ግለሰቦች የምስጋና የምስክር ወረቀትና ልዩ የገንዘብ ሽልማት መበርከቱን ከመከላከያ ሠራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡