የሀገር ውስጥ ዜና

በሁሉም ማዕዘናት የኢትዮጵያን የቱሪዝም ሐብት ለማስተዋወቅ እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ

By ዮሐንስ ደርበው

December 25, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በአራቱም አቅጣጫዎች ያላትን ተዝቆ የማያልቅ የቱሪዝም ሐብት ለማስተዋወቅ መንግሥት በልዩ ትኩረት እየሠራ መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባሕል፣ ማራኪ መልከዓ-ምድር፣ የተለያየ ዝርያ ያላቸው የዱር እንስሳት፣ ፍል ውኃዎች፣ ፏፏቴዎች በአጠቃላይ ውብ ተፈጥሮ የታደለች መሆኗን የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ ገልጸዋል፡፡

እነዚህን ለበርካታ ዓመታት የኖሩ ፀጋዎችም እንደ ሀገር በሚፈለገው ልክ ጥቅም ላይ አለመዋላቸውን ጠቅሰው÷ አሁን ግን መንግሥት ለቱሪዝም ልዩ ትኩረት በመስጠቱ የጎብኚ መዳረሻዎችን እያለማ ነው ብለዋል፡፡

የመስኅብ ስፍራ መኖር ብቻ በቂ አይደለም ያሉት ሚኒስትሯ÷ ደረጃቸውን የጠበቁ መዳረሻዎች፣ ማረፊያዎች እና የቱሪዝም መሠረተ-ልማቶች እንደሚያስፈልጉ አስገንዝበዋል፡፡

ከዚህ አንጻርም እንደ አዲስ በርካታ ሥራዎች መጀመራቸውን ጠቁመው÷ በገበታ ለሸገር፣ በገበታ ለሀገር የተገነቡትን እና በገበታ ለትውልድ አማካኝነት ደግሞ እየተገነቡ ያሉትን በርካታ ሥራዎችን ጠቅሰዋል፡፡

እነዚህም እንደሀገር ያሉንን የቱሪዝም ምርቶች እና መዳረሻዎች ከማብዛት አንጻር ከፍተኛ ሚና አላቸው ነው ያሉት፡፡

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት የቱሪዝም መዳረሻ እንዳልነበረው ጠቅሰው፤ አሁን ላይ ግን በኮይሻ ፕሮጀክት አመካኝነት የቱሪስት መዳረሻ መገንባቱን አንስተዋል።

ቀደም ሲል ወደ የጨበራ ጩርጩራ ፓርክ መግባት አይቻልም ነበር፤ አሁን ግን የቱሪዝም መሠረተ ልማቶች በመሟላታቸው ለጎብኚ ምቹ ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡

የጨበራ የዝሆን ዳና ሎጅም ዘመናዊ ሆኖ ከተፈጥሮ ጋር ተጣጥሞ የተሠራ ልዩ መዳረሻ ነው ያሉት አምባሳደር ናሲሴ÷ ጎብኚዎች ወደዚህ ሥፍራ ቢመጡ ሁሉንም በአንድ ቦታ ማግኘት እንደሚችሉ አመላክተዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!