አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቱሪዝም ዘርፉ እየታዩ ያሉ እንቅስቃሴዎች የግሉን ዘርፍ የሚያነቃቁ ናቸው ሲሉ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡
ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ለምረቃ የበቃውን የጨበራ የዝሆን ዳና ሎጅ አስመልክቶ እንዳሉት ኢትዮጵያ ጥልቅ የቱሪዝም ሃብት ያላት ነገር ግን በሃብቷ መጠን ከቱሪዝም ዘርፍ ያልተጠቀመች ሀገር ናት፡፡
በርካታ ሀገራት የኢትዮጵያን ያክል ሃብት ሳይኖራቸውን ከቱሪዝም ዘርፍ ተጠቃሚ እንደሚሆኑም አንስተዋል፡፡
ይህም ትክክል አለመሆኑን ያመነ እይታ ያለው አዲስ የኢኮኖሚ ሪፎርም ታስቦ በተለይ በሃገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው አምስት የእድገት ምንጮች መለየታቸውን እና ከዚህም ውስጥ ቱሪዝም አንዱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ይህም የሆነው ዘርፉ የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡
ለምረቃ የበቃው የጨበራ የዝሆን ዳና ሎጅ ከመልማቱ በፊት መስህቡ እና አካባቢው የሚያምር ገፅታ ቢኖረውም መዳረሻ ስላልነበረው ጎብኚ ሊመጣ የማይችልበት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
አሁን ግን መሰረተ ልማት ተሟልቶለት በዚህ ሁኔታ መሰራቱን ጠቅሰው ይህም ተኝቶ የነበረውን ዘርፍ እንደ ማንቃት ነው ብለዋል፡፡
ሎጂው የስራ ዕድል በመፍጠር ለሀገር ኢኮኖሚ የራሱን አስተዋፅኦ የሚያበረክትና የውጭም ሆነ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን እንደሚስብ በመጥቀስም፥ አዳዲስ እይታን በመፍጠር ሌሎች ንግዶችን የሚፈጥርና የሚያነቃቃ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡