አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ ተጠልለው ለሚገኙ ስደተኞች ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንዲያደርግ የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ጥሪ አቀረበ፡፡
ኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ስደተኞች ተቀብላ እያስተናገደች ቢሆንም ዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች የሚያደርጉት ድጋፍ አነስተኛ መሆኑንም ነው አገልግሎቱ ያስታወቀው፡፡
አሁን ላይ ኢትዮጵያ ከ1 ሚሊየን በላይ ስደተኞችንና ተገን ጠያቂዎችን ተቀብላ እያስተናገደች መሆኗን የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሙሉዓለም ደስታ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ስደተኞችን ተቀብሎ ከመመዝገብና መጠለያ እንዲያገኙ ከማድረግ ጀምሮ የሚጠበቅባትን ኃላፊነት እየተወጣች መሆኗም ገልጸዋል፡፡
በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ ሰባት የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች በስደተኞችና በተቀባይ ማኅበረሰቡ የጋራ ፕሮጀክት ውጤታማ የልማት ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል፡፡
ባለፉት ሦስት ወራት ኢትዮጵያ 16 ሺህ ለሚሆኑ ስደተኞች የሥራና የመኖሪያ ፈቃድ በመስጠት ከተቀባዩ ማኅበረሰብ ጋር በተለያዩ የልማት ሥራ እንዲሰማሩ ማስቻሏንም ነው የገለጹት፡፡
አሁን ላይ የአጋር አካላት ድጋፍ እየተቀዛቀዘ መምጣቱን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፥ በሱዳን ግጭት ምክንያት በመተማና ኩምሩክ በኩል ወደ ኢትዮጵያ ለገቡ ከ42 ሺህ በላይ ሱዳናውያን የሚደረገው አፋጣኝ ሰብዓዊ ድጋፍ ላይ ክፍተት መፈጠሩን አንስተዋል፡፡
ዓለም አቀፍ ረጂ አካላትም ስደተኞች ሰብዓዊ መብታቸው ተጠብቆ መሠረታዊ አቅርቦት እንዲያገኙ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንዲያደርጉ ተጠይቀዋል፡፡
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!