የሀገር ውስጥ ዜና

ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) የሕዝቦችን ትስስር በይበልጥ ማጎልበት እንደሚገባ ገለጹ

By ዮሐንስ ደርበው

December 26, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝቦችን ጠንካራ ትስስር በይበልጥ በማጎልበት በአጎራባች ክልሎች ወሰን አካባቢ የሚከሰቱ የወሰን ጉዳዮችን በጋራ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ መፍታት እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) አስገነዘቡ፡፡

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልልና በጋምቤላ ክልል በጋራ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ውይይት በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ነው።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ሠላምና ልማት የማይነጣጠሉ የመንግስትና የማህበረሰብ የጋራ ትብብር ውጤት መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ሠላምን በማጽናት የማኅበረሰቡን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብሮች በማሳለጥ የልማት ዐቅምን በተጨባጭ ማሣደግ ይጠበቅብናል ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል፡፡

ለዚህም የሁለቱን ክልሎች ሕዝቦች የእርስበርስ ትስስር በይበልጥ እንዲጎለብት በማድረግ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ባሕላዊ እሴቶችን ማሣደግ ላይ ማተኮር ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡

የውስጥ ጉዳዮቻችንን በጋራ በመፍታት ሕገ-ወጥ የማዕድንና ሌሎች የምርት ንግድና ኮንትሮባንድ፣ ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን መከላከል የዘወትር ሥራዎቻችን ሊሆኑ ይገባልም ብለዋል፡፡

የሁለቱ ክልል ሕዝቦች በተመሳሳይ የመልክዓ-ምድር አቀማመጥ፣ የዓየር ጸባይ እንዲሁም በርካታ የጋራ እሴቶችን የሚጋሩ መሆናቸውንም አብራርተዋል፡፡

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!