የሀገር ውስጥ ዜና

በትግራይ ክልል 800 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እየተሰራጨ ነው

By ዮሐንስ ደርበው

December 26, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለበጋ መስኖ ልማትና ለ2016/17 ምርት ዘመን አገልግሎት የሚውል 800 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እየተሰራጨ መሆኑን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እርሻና ገጠር ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው ኃላፊ ኢያሱ አብርሃ (ዶ/ር) እንዳሉት÷ የፌደራል መንግሥት ባመቻቸው 6 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ብድር የተገዛው የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ እየተሠራጨ ነው፡፡

እስካሁንም በሁለት ዙሮች በሚከናወነው የበጋ መስኖ ሥራ 120 ሺህ ሔክታር መሬት የሚለማ ሲሆን÷ ለዚሁ የሚውል 87 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ተከፋፍሏል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም በ2016/17 ምርት ዘመን የሚያስፈልገው ማዳበሪያ ወደ ክልሉ መግባት መጀመሩን ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቅት የማዳበሪያ ችግር አለመኖሩን ገልጸዋል።

አርሶ አደሩ ከወረዳው የፈለገውን መጠንና ዓይነት ማዳበሪያ መጠቀም እንደሚችል መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በሌላ በኩል በጊዜያዊ አስተዳደሩ በተለያዩ ምክንያቶች ተቋርጦ የቆየውን የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ በየካቲት ወር ለማስጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በሥራው ከግማሽ ሚሊየን በላይ ሕዝብ በነፃ ይሳተፋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የገለጹት ኃላፊው÷ በሦስት ተፋሰሶች ላይ እርከኖችና ሌሎች የአፈርና ውሃ ጥበቃ ተግባራት እንደሚከናወኑ አመላክተዋል፡፡

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!