አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀሰተኛ የሆነ የመጀመሪያ ዲግሪ የትምህርት ማስረጃ በመጠቀም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አምቦ ዲስትሪክት የስራ ቅጥር ፈጽመዋል የተባሉ ግለሰቦች በእስራት እንዲቀጡ የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወንጀል ችሎት ወሰነ።
ተከሳሾቹ ወንጀሉን መፈጸማቸውን አምነው ለችሎቱ ቃላቸውን መስጠታቸውን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ ተጨማሪ ማስረጃ መስማት ሳያስፈልገው በተከሳሾቹ ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፏል።
የኦሮሚያ ክልል ፍትህ ቢሮ የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ የሙስና አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 23 ስር የተመላከተውን ድንጋጌን ተከሳሾቹ ተላልፈዋል በማለት ሀሰተኛ መንግስታዊ ወይም ህዝባዊ ሰነዶችን አዘጋጅቶ መጠቀም የሙስና ወንጀል ክስ አቅርቦባቸው ነበር።
ክሱ የቀረበባቸው ተከሳሾች በአጠቃላይ 12 ሲሆኑ፤ ከነዚህ መካከል ባጂጌ ከበደ፣ ግርማዬ ደገፉና በሬዳ ነበራ ይገኙበታል።
የቀረበው ክስ ላይ እንደሚያመላክተው ተከሳሾቹ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አምቦ ዲስትሪክት በወጣ የስራ ማስታወቂያ የመጀመሪያ ዲግሪ የትምህርት ማስረጃ በማቅረብ የስራ ቅጥር ውል ስምምነት መፈጸማቸው በክሱ ተጠቅሷል።
ከተከሳሾቹ መካከል 10ሩ የቅጥር ውል ከፈጸሙ በኋላ ለ10 ወራት በየደረጃው በተለያዩ መጠን ወርኃዊ ደመወዝ መውሰዳቸውን ዐቃቤ ሕግ በክሱ አመላክቷል።
ቀሪዎቹ ማለትም ሁለት ተከሳሾች ደግሞ የስራ ቅጥር ውል ስምምነት ከፈጸሙ በኋላ የማስረጃ ማጣራት ስራ ሲጀመር መሰወራቸው ዐቃቤ ሕግ በክሱ አመልክቷል።
በዚህም መልኩ ዐቃቤ ሕግ ሀሰተኛ መንግስታዊ ወይም ህዝባዊ ሰነዶችን አዘጋጅቶ መጠቀም የሙስና ወንጀል ክስ አቅርቦባቸዋል።
የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወንጀል ችሎት በተከሳሾቹ ላይ የቀረበው ክስ ዝርዝር ለተከሳሾቹ እንዲደርስ በማድረግ የክስ ዝርዝሩ በችሎት በንባብ አሰምቶ ነበር።
ዐቃቤ ሕግ ከክሱ ጋር ለወንጀሉ መፈጸም ያስረዱልኛል ያላቸውን የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን አያይዞ አቅርቧል።
የዋስትና መብታቸው ታግዶ ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ ብይን የተሰጠባቸው ተከሳሾቹ በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን ተከታትለዋል።
በዐቃቤ ሕግ የቀረበባቸው የክስ ዝርዝር እንዲሻሻልላቸው ተከሳሾች የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ ቢያቀርቡም፤ ዐቃቤ ሕግ ክሱ ግልጽ መሆኑን ጠቅሶ ሊሻሻል አይገባም የሚል መልስ በጽሁፍ አቅርቧል።
ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን መርምሮ የክስ መቃወሚያ ጥያቄው ክሱ እንዲሻሻል የሚያስችል የህግ መሰረት የለውም በማለት ውድቅ አድርጓታል።
ከዚህም በኋላ ተከሳሾቹን የዕምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ ተደርጎ ተከሳሾቹ የወንጀል ተግባሩን መፈጸማቸውን አምነው ለችሎቱ ቃላቸውን ሰጥተዋል።
በዚህም ፍርድ ቤቱ ተጨማሪ ምስክር መስማት ሳያስፈልገው በተከሳሾቹ ላይ በተከሰሱበት ድንጋጌ የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፎባቸዋል።
ተከሳሾቹ በክሱ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት በማመናቸው፣ የቀደመ የወንጀል ሪከርድ አለመኖሩንና የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸውን በቅጣት ማቅለያ ታሳቢ በማድረግ ፍርድ ቤቱ እያንዳንዳቸውን በ1 አመት ከ 8 ወራት እስራት እንዲቀጡ ወስኗል።
በታሪክ አዱኛ