የሀገር ውስጥ ዜና

አቶ ጥላሁን ከበደ በጎፋ ዞን የልማት ሥራዎችን እየጎበኙ ነው

By Melaku Gedif

December 27, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በጎፋ ዞን ኦይዳ ወረዳ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ሥራዎችን እየጎበኙ ነው፡፡

በጉብኝታቸውም በአካባቢው እየተሰሩ ያሉ የሌማት ትሩፋት አካል የሆኑ የግብርና ምርት ውጤቶችን በአርሶ አደሮች ማሳ ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

በዚህም በአርሶ አደሮች ማሳ ያሉ የሰብል ምርት የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ፣ የሙዝ ማሳ፣ የእንስሳት ተዋጽኦ ውጤቶች እና የንብ እርባታ ሥራን ጎብኝተዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን በወቅቱ እንዳሉት÷ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የተጀመሩ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብሮች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው፡፡

አርሶ አደሮች በኩታ ገጠም ተደራጅተው የተሻለ ምርት ማምረት እንዳለባቸው ጠቅሰው÷ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡

አርሶ አደሮች በበኩላቸው÷ የገበያ ትስስር እንዲፈጠር እና የመሠረተ ልማት ማሟላት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ መጠየቃቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡