የሀገር ውስጥ ዜና

በጠለፋና አስገድዶ መድፈር የተከሰሰው ሳጅን የኋላመብራቴ ወ/ማሪያም በእስራት ተቀጣ

By Mikias Ayele

December 28, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የግል ተበዳይ የሆነችውን ፀጋ በላቸውን በመጥለፍ እና አስገድዶ በመድፈር የወንጀል ድርጊት የተከሰሰው ሳጅን የኋላመብራቴ ወ/ማሪያም ላይ በእስራት እንዲቀጣ ተወሰነ።

የሲዳማ ክልል ፍትህ ቢሮ እንዳስታወቀው÷ ሳጅን የኋላመብራቴ በቀን 12/02/2016 ዓ.ም የግል ተበዳይ የሆነችውን ፀጋ በላቸውን በመጥለፍና አስገድዶ በመድፈር የተከሰሰበት መዝገብ በሀዋሳ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቀርቦ ሲያከራክር መቆየቱን ገልጿል፡፡

ፍርድ ቤቱ የከሳሽ ዓቃቤ ህግ ያቀረበውን ማስረጃ በመስማት ተከሳሽ በ1ኛ ክስ የወንጀል ህግ አንቀፅ 37 እና 587(1) መሰረት እንዲከላከል እንዲሁም በሁለተኛ ክስ  በ620 (3) መሰረት እንዲከላከል ብይን ቢሰጥም ተከሳሽ ጥፋቱን ባለማስተባበሉ ፍ/ቤቱ ተከሳሹን ጥፋተኛ ብሎታል፡፡

በዚሁ መሰረትም የሀዋሳ ከተማ መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በቀን 18/04/2016 ዓ.ም በዋለው የሴቶችና ህጻናት ችሎት የቅጣት ማክበጃ እና ማቅለያ ሁኔታዎችን በማየት በተከሳሹ ላይ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

በውሳኔው መሰረትም ተከሳሽ ሳጅን የኋላመብራቴ ወ/ማሪያምን በ16 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ የተወሰነበት መሆኑን ከሲዳማ ክልል ፍትህ ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡