አዲስ አበባ፣ ታኀሣስ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል እያሳየ መሆኑን የሰሜን ምዕራብ ዕዝ አዛዥና የኮማንድ ፖስቱ ሰብሳቢ ሌ/ጄ ብርሃኑ በቀለ ተናገሩ።
ኮማንድ ፖስቱ ከክልል፣ ከዞንና ከወረዳ አመራሮች እንዲሁም ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የፀጥታና የደህንነት ኃላፊዎች ጋር በቀጣናው ወቅታዊ ሁኔታ ላይ በጎንደር ከተማ ተወያይቷል፡፡
ሌ/ጄ ብርሃኑ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ በክልሉ የተገኘውን አንፃራዊ ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠል በየደረጃው የሚገኙ የአስተዳደርና የፀጥታ አካላት ኃላፊነታቸውን በቁርጠኝነት እንዲወጡ ማድረግ ይገባል፡፡
በአማራ ክልል ተከስቶ የነበረው የፀጥታ ችግር በሠራዊቱ ስኬታማ የግዳጅ አፈፃፀምና በህብረተሠቡ የተቀናጀ ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል እያሳየ መምጣቱንም አንስተዋል፡፡
መከላከያ ሠራዊት ጥበብ በተሞላበት የግዳጅ አፈፃፀም ክልሉን በማፍረስ የብጥብጥና የትርምስ ቀጠና ለማድረግ ሲጥሩ የነበሩ ፅንፈኛ ኃይሎችን ሴራ ማክሸፍ ችሏል ነው ያሉት፡፡
የፅንፈኛው ቡድን ዓላማና ተግባር የአማራን ህዝብ ስቃይ ማራዘም፣ ህዝቡንተስፋ ማስቆረጥ፣ የልማት አውታሮችን ማውደምና እንዲዳከሙ ማድረግ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
የክልሉ ህዝብ የፅንፈኛውን ቡድን ሴራ በመገንዘብ ከፀጥታ ኃይሉ ጋር ተቀናጅተው መዋቅሮችን የማጥራት እንዲሁም አቅማቸውን የማጠናከር ስራ በመስራት ዘላቂ ሰላም ማስፈን ይገባል ማለታቸውንም የመከላከያ ሠራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ መረጃ ያመላክታል፡፡