የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ለአምስት ዓመታት የሚያገለግል የቆጣሪ ውል እድሳት ጀመረ

By Melaku Gedif

December 28, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ለቀጣይ አምስት ዓመታት የሚያገለግል የቆጣሪ ውል እድሳት ማድረግ መጀመሩን አስታውቋል፡፡

ይህን ተከትሎ ከኅዳር 1 እስከ ታኅሣሥ 16 ቀን 2016 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ 100 ሺህ ደንበኞች ውላቸውን ማደሳቸው ነው የተገለጸው፡፡

የውል እድሳቱ ለደንበኞች ቀልጣፋ አገልግሎትና ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች በቀላሉ ምላሽ መስጠት ያለመ ነው ተብሏል።

አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ቆጣሪዎችን ለማወቅና አዳዲስ ቆጣሪዎችን ለደንበኞች ለመስጠት እንደሚያስችልም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር መላኩ ታዬ እንደገለጹት÷ የውል እድሳቱ ዓላማ ደንበኞችን በሚገባ ማወቅና የደንበኞችን ፍላጎት መሠረት ያደረገ አገልግሎት መስጠት ነው።

ቆጣሪን ለማይታወቅ አካል የሚያስተላልፉ ደንበኞችን ለመቆጣጠርና የኃይል ሥርቆትን ለማስቀረት እንዲሁም የኃይል መቆራረጥ ችግር ለማቃለል እንደሚያስችል አመልክተዋል።

ደንበኞች እስከ መጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ በተቋሙ ቅርንጫፎች በመገኘት ውላቸውን እንዲያድሱ ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ውል ከፈፀሙ አምስት ዓመት የሞላቸው ደንበኞች እንዲያድሱ የሚገደዱ ሲሆን÷ አዲስ የሚያድሱት ውል ደግሞ ለአምስት ዓመት የሚቆይ እንደሆነ አብራርተዋል።

#Ethiopia ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!