አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካቢኔ ባካሄደው ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።
የክልሉ ካቢኔ በመጀመሪያ በምግብ እና መድሐኒት አስተዳደር ረቂቅ ደንብ አጀንዳ ዙሪያ ተወያይቷል።
የምግብና መድሐኒት አስተዳደር ረቂቅ ደንብ በክልሉ በግል የጤና ተቋማት የሚስተዋለውን የመድሐኒት አጠቃቀም፣ በሰው ልጆች ላይ የሚያደርሰውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመቀነስ ታልሞ እንደተዘጋጀ ተገልጿል፡፡
በረቂቅ ደንቡ አስፈላጊነትና አተገባበር ላይ ውይይት ያካሄደው የክልሉ ካቢኔ የምግብ እና የመድሐኒት አስተዳደር ረቂቅ ደንብ ሆኖ ወደ ስራ እንዲገባ ወስኗል።
በሌላ በኩል የክልሉ ካቢኔ በክልሉ የምግብ ስርዓትና ስርዓተ-ምግብ ምክር ቤት ማቋቋሚያ ረቂቅ ደንብ ላይ መወያየቱን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
የክልሉ የምግብ ስርዓትና ስርዓተ ምግብ ምክር ቤት ማቋቋሚያ ረቂቁ በክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የሚመራ እና ረቂቅ ደንቡ እስከታችኛው መዋቅር ተደራሽ ተደርጎ ወደ ስራ እንዲገባም ካቢኔው ውሳኔ አሳልፏል፡፡