አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አባበ ከተማን አገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋና ፍትሐዊ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የከተማዋ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡
ከተማ አስተዳደሩ ከህብረተሰቡ ጋር ባካሄዳቸው ውይይቶች የአገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋ፣ ከብልሹ አሰራርና ከሌብነት የጸዳ ማድረግ እንደሚገባ ከሕዝቡ በጥያቄ መነሳቱ ተጠቅሷል፡፡
በዚህ መሰረትም አገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል የከተማ አስተዳደሩ በልዩ ትኩረት እየሠራ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ሃላፊ ጣሰው ገብሬ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ አገልግሎት አሰጣጡን ከከተማዋ ዕድገትና ከሕዝቡ ፍላጎት ጋር የሚመጣጠን ለማድረግ የዲጂታላዜሽን አገልግሎት መስጠት በመጀመሩ ለውጦች መታየት መጀመራቸውን አንስተዋል፡፡
አገልግሎት አሰጣጡን ከብልሹ አሰራር የጸዳና ይበልጥ ቀልጣፋ ለማድረግ የሚያስችል ጥናት ተጠንቶ የአሰራርና የአደረጃጀት ለውጦች መደረጋቸውንም ጠቁመዋል፡፡
በጸደቀው አደረጃጀት መሠረት ብቁ ስነ-ምግባር ያለው የሰው ኃይል ለመፍጠር የክህሎትና የስነ ምግባር ክፍተቶችን መለየትና ክፍተቶቹን የሚደፍኑ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን መስጠት የሚያስችል ምዘና እንደሚካሄድም ጠቅሰዋል፡፡
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የስራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥራቱ በየነ በበኩላቸው÷ የከተማው ነዋሪ በሚፈልገው መጠን አገልግሎት እያገኘ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ የተቋማትን አገልግሎት አስመልክቶ ባካሄደው ጥናትና በተለያዩ ህዝባዊ ውይይቶች አገልግሎቱ መሻሻል እንዳለበት ያሳየ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በዚህም ከተፈለገው ክህሎትና የሥነ ምግባር ክፍተቶችን መለየትና ክፍተቶችን የሚደፍኑ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን መስጠት የሚያስችል ምዘና እንደሚካሄድ የከንቲባ ጽ/ ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡
ከዳይሬክተር እስከ ፈጻሚ ድረስ ያሉ የመዲናዋ ሰራተኞች የሚሳተፉበት ምዘና በነገው ዕለት እንደሚሰጥ አቶ ጥራቱ ጠቁመዋል፡፡
በምዘናው በክህሎትና ስነ ምግባር አንጻር ክፍተት የተገኘባቸው ሰራተኞች በሚመጥኗቸው ቦታዎች ላይ በመመደብ ተገቢው የክህሎትና ስነ ምግባር አቅም ግንባታ ማሻሻያ ስልጠና እንደሚሰጥ አረጋግጠዋል፡፡