ጤና

በጤና ተቋማት የሚታየውን የደም እጥረት ለማቃለል ሕብረተሰቡ ደም እንዲለግስ ተጠየቀ

By Melaku Gedif

December 30, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጤና ተቋማት በደም አቅርቦትና ፍላጎት መካከል የሚታየውን ልዩነት ለማጥበብ ህብረተሰቡ ደም የመለገስ ተግባሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች የሚገኙ የደም ባንክ ሃላፊዎች ጠየቁ።

በኦሮሚያ ጤና ቢሮ የጎባ ደም ባንክ ዳሬክተር ሰለሞን ገዛኸኝ ÷ የጎባ ደም ባንክ ባለፉት 5 ወራት ባደረገው የሥራ እንቅስቃሴ መሰብሰብ ከነበረበት 2 ሺህ ዩኒት ደም 1ሺህ 200 ዩኒት ደም ብቻ መሰብሰቡን ተናግረዋል፡፡

ደም ባንኩ በተያዘው የበጀት ዓመት ከ8 ሺህ ዩኒት በላይ ደም ከበጎ ፍቃደኞች ለማሰባሰብ አቅዶ ወደሥራ መገባቱን አስታውሰው÷ ባንኩ ከበጎ ፍቃደኞች እየሰበሰበ የሚገኘው ደምና በየጤና ተቋማት ያለው የደም ፍላጎት እንደማይጣጣም ጠቁመዋል።

በአማራ ክልል ካለው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ የበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች ቁጥር መቀነስ በሚፈለገው ልክ ደም ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ደም ሰብስቦ ማሰራጨት አለመቻሉን የክልሉ ጤና ቢሮ ገልጿል።

በቢሮው የክልሉ ደም ባንክ አስተባባሪ አቶ አንዳርጌ አጥናፉ ÷በበጀት ዓመቱ በክልሉ 107 ሺህ ዩኒት ደም ከበጎ ፈቃደኞች ለመሰብሰብ ቢታቀድም ባለፉት አምስት ወራት ተሰብስቦ የተሰራጨው ደም ከ14 ሺህ ዩኒት እንደማይበልጥ ገልጸዋል።

በዕቅዱ መሰረት ከበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች በመሰብሰብ ደም ለሚያስፈልጋቸው ወላድ እናቶችና ቀዶ ህክምና ለሚያደርጉ ወገኖች ተደራሽ ማድረግ አለመቻሉን ተናግረዋል።

በዚህም በክልሉ የሚገኙ ጤና ተቋማት በደም አቅርቦት እጥረት እየተፈተኑ እንደሚገኙ ነው የገለጹት፡

በተመሳሳይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የዲላ ደም ባንክ ስራ አስኪያጅ ሲስተር መሰረት ዘውዴ እንዳሉት÷ ከጊዜ ወደ ጊዜ ደም የመለገስ ባህል እየደገ ቢመጣም የሚፈለገውን ያህል አይደለም ።

በማዕከሉ በወር ከ333 ዩኒት በላይ ደም ለመሰብሰብ ቢታቀደም በየወሩ በአማካይ የሚሰበሰበው ከ50 በመቶ ያነሰ መሆኑን ገልጸው÷ ይህም የጤና ተቋማትን የደም ፍላጎት ለማሟላት አዳጋች እንዳደረገው ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ደም በመለገስ የሰውን ሕይወት በተለይ የእናቶችንና ህጻናትን ስቃይ በመቀነስ የአዕምሮ እረፍትና እርካታ የሚያስገኝ በመሆኑ ህብረተሰቡ ደም በመለገስ ሕይወት እንዲያድን ሃላፊዎች ጥሪ አ